በፍትህ ተቋማት ላይ ለተደረጉት ማሻሻያዎች ተፈጻሚነት የሁሉም አካላት ጥረትና የህዝቡ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል

67

አዲስ አበባ የካቲት 08/2014(ኢዜአ) በፍትህ ተቋማት ላይ ለተደረጉት ማሻሻያዎች ተፈጻሚነት የሁሉም አካላት ጥረትና የህዝቡ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ::

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የፍትህ ስርዓቱ አጋዥ የሆኑ የተለያዩ ህጎች መሻሻላቸው ይታወቃል።

ማሻሻያዎቹ በአገሪቱ ለሰብዓዊ መብት መከበርና የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ሚናቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ይነገራል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በተደረጉት የህግ ማሻሻያዎች ዙሪያ ያነጋገርናቸው የህግ ባለሙያዎች ማሻሻያው የፍትህ ተቋማቱ የተሻለ አቅም እንዲኖራቸው እና ህገ-መንግስታዊ ሃላፊነቶቻቸውን በተገቢው መንገድ እንዲወጡ ያደርጋልም ብለዋል።

የህግ ባለሙያው አቶ አዲ ድኬቦ እንዳሉት በፌዴራል ፖሊስ ላይ የተደረገውን ማሻሻያ ከዚህ ቀደም በማህበረሰቡና በሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ዘንድ የነበረውን ስም ያደሰ ነው ብለዋል፡፡

ከለውጡ በፊት በምርመራ እና በወንጀል መከላከል ሂደቶች በሰዎች ላይ የተለያዩ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ይፈጸሙ እንደነበር አስታውሰው በተደረገው ማሻሻያ በሰብአዊ መብት አያያዝ ተጨባጭ ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል።

በተቋሙ የሚታዩ አዎንታዊ ሂደቶች ቀጣይነት ሊኖራቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር እና ጠበቃ የሆኑት አቶ ቸርነት ሆርዶፋ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት መንግስት ኢትዮጵያዊ ባለሙያዎች እንዲሳተፉ በማድረግ ህጎችን በማሻሻል ረገድ ሰፊ ስራ ሰርቷል ብለዋል፡፡

በተለይ በፍትህ ተቋማት ዘንድ በርካታ አዋጆች መጽደቃቸው እና ሌሎችም በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በፍትህ ተቋማት ዘንድ የተሰራው ስራ ከፍተኛ ቢሆንም ህዝቡ ጋር ከመድረስ አንጻር ግን ውስንነት የሚታይባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም በቀጣይ ለማሻሻያዎቹ ተፈጻሚነት የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ መረባረብ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ 

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለሶስት ዓመታት በተደረጉት የህግ ማሻሻያዎች ዙሪያ ሲካሄድ የነበረው ውይይትም ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም