"አሸባሪው ህወሃት ለስራ የማይታክቱ እጆቻችን ላይ ያደረሰው ጉዳት ሰርተን እንዳንበላ አድርጎናል"

126

የካቲት 8 ቀን  2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ለስራ የማይታክቱ እጆቻችን ላይ ያደረሰው ጉዳት ሰርተን እንዳንበላ አድርጎናል ሲሉ አባትና ልጅ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

አርሶ አደር አያሌው ገብረየስ የሚኖሩት በአማራ ከልል ሰሜን ወሎ ዞን ዞብል አቅራቢያ ነው።

የጠንካራ ገበሬ ተምሳሌት የሆኑት አርሶ አደር አያሌው ከማለዳ እስከ ምሽት ኑሮን ለማሸነፍ ቤተሰቦቻቸውን ለመምራት ሲሉ ሳይታክቱ ስራቸውን በማከናወን ይታወቃሉ።

የግብርና ስራ ከወቅቶች ጋር ሽቅድምድም በመሆኑ የእርሻና የዘር ወቅቶች እንዳያልፉ ከመትጋት በስተቀር ለሌሎች ጉዳዮች ትርፍ ጊዜ እንደሌላቸው ይናገራሉ።

በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ ፈፅሞ የቆየው አሸባሪው ህወሃት በደረሰባቸው አካባቢዎች  ዘረፋና ውድመት አድርሷል፣ በርካታ ንጹሃንን በመግደልና የአካል ጉዳት በማድረስ የጭካኔ ጥጉን አሳይቷል።

አርሶ አደር  አያሌው ገብረየስና ልጃቸው ተስፋ አያሌው፤ የዚሁ አሸባሪ ቡድን ሰለባ ሆነው  በአዲስ አበባ ጦር ሃይሎች ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል ህክምና ሲከታተሉ አግኝተናቸዋል።

አርሶ አደር  አያሌው  ስለ ሆነውና ስላጋጠማቸው ነገር በዝርዝር ይናገራሉ።

አሸባሪው ህወሃት አካባቢውን ከወረረ በኋላ ለዘረፋና ግድያ ያባከነው ጊዜ እንደሌለ የሚናገሩት አርሶ አደሩ፤ ያላችሁን አምጡ! በማለት ያገኙትን እየቀሙና እየዘረፉ፤ ያሻቸውን ሰው እየገደሉና እያቆሰሉ መቆየታቸውን ይናገራሉ።

በዚሁ ሁኔታ እርሳቸውና የ14 ዓመት ታዳጊ ልጃቸው ተስፋ አያሌው፤ የዚሁ አሸባሪ ቡድን የጭካኔ በትር አርፎባቸው ለከባድ የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት ህዝብ ለማደናገር በቃል "የምንዋጋው ከፖለቲከኞች ጋር እንጂ ከአርሶ አደሮች ጋር ቂምና ጥላቻ የለንም" በማለት በተግባር ግን አጠቃላይ የህዝብ ጠላት መሆኑን የሚያሳዩ አርሶ አደር አያሌውና ልጃቸውን የመሰሉ ተጎጂዎች እንዲሁም ለሞት የተዳረጉ በርካቶች ናቸው።

አባትና ልጁ የጥይት ሰለባ የሆኑበት አጋጣሚ ከግብርና ስራቸው ወደ መኖሪያቸው እንደተመለሱ የአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች ወደ ቤት ዘልቀው በመግባት ውሃ አምጡ በሚል ሰበብ የእሩምታ ተኩስ  እንደከፈቱባቸው ያስታውሳሉ።

ከአሸባሪዎቹ ጥቃት ከቤት ወጥተው በማምለጥ ህይወታቸውን ለማትረፍ ጥረት ባደረጉበት አጋጣሚ በማሳደድ በእጆቻቸው ላይ ላይ ከባድ አደጋ አድርሰውባቸዋል።

በአሸባሪዎቹ የጭካኔ በትር ሰርተን እንዳንበላ እጅና እግራችንን እየሰበሩ፣ ልጆቻችንን እንዳይደግፉን የፈለጉትን ገድለው፣ ሌላውን አካሉን እያጎደሉ የጥላቻቸውን ጥግ አሳይተውናል ይላሉ አርሶ አደር አያሌው።

''እኔ አርሶ አደር ነኝ ከፖለቲካ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለኝም ሆኖም እኔንም ቤተሰቤንም በግፍ ተኩሰው በመምታት ለከፍተኛ ጉዳት ዳርገውናል" ብለዋል።

መከላከያ ከወደቁበት በማንሳት በጦር ሃይሎች ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓቸዋል።

ሆኖም ለስራ በማይታክቱ እጆቻቸው ላይ ባደረሱባቸው  ጥቃት '' አሸባሪዎች ተራምደንና ሰርተን ለመብላት እንዳንችል አድርጎናል" ብለዋል።

በተለይም መከላከያ አካባቢውን ሲቆጣጠር መሸነፋቸውን በአግባቡ ስለተረዱ በርካታ ነዋሪዎችን ገድለው መሄዳቸውን ገልጸዋል።

‘’እናንተ አርሶ አደር ናችሁ ከእናንተ ጋር ጸብ የለንም ሲሉ ቆይተው ፀባቸው ከእኛ መሆኑን በተግባር አሳይተውናል" ሲሉ አርሶ አደር አያሌው ተናግረዋል።

በአካባቢያችን የአሸባሪው ቡድን አባላትም መከላከያውም ቆይተው አይተናል  የሁለት ዓለም ሰዎች ናቸው አሸባሪው ደፋሪና ለሰው ደንታ የሌለው መከላከያ ደግሞ ለሰው ልጅ የሚራራ የወደቀን የሚያነሳ መሆኑን አይተናል።

በአካባቢያችን በአሸባሪው ህወሃት ተጎድተው ህክምና ሳያገኙ ቆይተው የሞቱ አሉ የሚሉት አርሶ አደር አያሌው እኛ እድለኛ ሆነን ደማችን ፈስሶ ሳያልቅ ህይወታችንን መከላከያ ታድጎናል ብለዋል።

‘’እኔ ደሃ ነኝ’’ ልሰጠው የምችለው ሃብት የለኝም የሚሉት አርሶ አደሩ ህይወቴን ላተረፈው መከላከያ ሰራዊት ግን ሕይወቴን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።

የጦር ሃይሎች ኮምፕሬንሲቭ እስፔሻላይዝ ሆስፒታል ለሰራዊቱ ከሚሰጠው ህክምና በተጓዳኝ ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም