በኢትዮጵያ ለቴኳንዶ ስፖርት የማዘውተሪያ ማዕከላትን በማስፋፋት ወጣቶችን ከሱስ ነጻ ማድረግ ይገባል

111

የካቲት 7/2014 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ የቴኳንዶና ሌሎች የስፖርት የማዘውተሪያ ማዕከላትን በማስፋፋት ወጣቶች ከሱስ ነጻ እንዲሆኑ ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት እንዳለበት የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ገለጸ።
የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቅሩ ተቋም፤ በኢትዮጵያ የቴኳንዶ ስፖርት ተወዳጅና ተዘውታሪ ስፖርቶች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ይናገራሉ።

ስፖርቱ በበርካታ ወጣቶች የሚፈለግ በመሆኑ በሁሉም አካባቢዎች የማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማመቻቸት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የቴኳንዶና ሌሎች የስፖርት የማዘውተሪያ ማዕከላትን በማስፋፋት ወጣቶች ከሱስ ነጻ እንዲሆኑ ለማስቻል በተለይም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በልዩ ትኩረት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

የቴኳንዶ ስፖርትን የሚያዘውትሩ ወጣቶችን አንዳንዶች በተሳሳተ መልኩ "ከድብድብ ጋር" የሚያያዙት እንዳሉ ጠቅሰው ስፖርቱ ግን መልካም ስብእና የሚያላብስ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም የቴክንዶ ስፖርት ወጣቶች ከሱስ ነፃ ሆነው ትእግስትን፣ ስነ- ስርአትን፣ ሰው አክባሪነትንና ታጋሽነትን እንዲላበሱ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ 674 የቴኳንዶ ስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች እንዳሉ አስታውስው በአማካኝ በእያንዳንዱ ማዘውተሪያ ቦታ 150 እስከ 200 ሰልጣኞች መኖራቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግን በቂ እና ምቹ ባለመሆናቸው በማስፋፋት በኩል ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በተለይም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በሁሉም አካባቢዎች የቴኳንዶ ማዘውተሪያ እንዲኖር ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።  

የስፖርቱን መስፋፋት በመደገፍ መልካም ትውልድ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረትም ከመንግስት አካላት በተጨማሪ ባለሃብቶችና ሌሎች ስፖርት ወዳዶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የቴኳንዶ ስፖርት የእጅ እና እግር እንቅስቃሴዎችን በማጣመር በተናጠለም ይሁን በቡድን የሚሰራ ተወዳጅ የስፖርት አይነት መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም