የማህበራዊ ሚዲያ አራማጆች የአማራ ህዝብን ፍላጎት የሚመጥን መረጃ ማድረስ አለባቸው...አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

185
ባህርዳር ነሀሴ 25/2010 የአማራ ማህበራዊ ሚዲያ አራማጆች ህዝቡ የሚፈልገውን ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ታላቅነቱን የሚመጥን መረጃ  በኃላፊነት እንዲያደርሱ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጠየቁ። “የአማራ ብሄርተኝነት ለጠንካራ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ በባህርዳር ከተማ ዛሬ የምክክር መድረክ ተካሒዷል። ርዕሰ መስተዳደሩ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት የአማራ ህዝብ ከጥንት እስከ ዛሬ ለሃገሩ፣ ለነፃነቱና ለፍትህ ሲታገልና መስዋትነት ሲከፍል ኖሯል። አሁን የተገኘው የነፃነት መንፈስ እንዲፈጠርና የለመለመ ተስፋ እንዲታይ ይህ ህዝብ ህይወቱን፣ ንብረቱንና አካሉን ሳይሰስት መስጠቱንም ተናግረዋል። "የለውጥ ጉዞው ህዝቡ የሚፈልገውን ነፃነትና የዴሞክራሲ ስርዓት እውን ለማድረግ የማህበራዊ ሚዲያ አራማጆችና ፖለቲከኞች ምክንያታዊ አስተሳሰብ በመገንባት በእውቀት የሚመራ እንቅስቃሴ እንዲዳብር ማድረግ ይገባል” ብለዋል። ህዝብን ከህዝብ ለመለያየት በተቀደደ ቦይ መፍሰስ ሳይሆን ህዝብን ከህዝብ የሚያቀራርቡ አዳዲስ መንገዶችን መገንባት እንደሚጠበቅባቸውም አብራርተዋል። ለሚያራምዱት ሃሳብም ከግብዝነት ነፃ በሆነ መንገድ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ሃሳቦችም የአማራን ህዝብ ታላቅነት የሚመጥኑ ይበልጥ የሚያስተሳስሩ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌደራሊዝምና ሰብአዊ መብት መምህር ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው እንደገለጹት አሁን የመጣው ጅምር ለውጥ ማህበራዊ ሚዲያው ወጣቱን ለትግል በማነሳሳቱ የተገኘ ድል ነው። "በማህበራዊ ሚዲያው ግልፅ አላማ አንግቦ በሃላፊነት መንፈስ በመስራት መልካም እሴት መገንባትና ለለውጥና እድገት ተግቶ መስራት ይገባል" ብለዋል። ህዝብን ከህዝብ ከሚያጋጩ፣ የሰዎችን ወይም የተወሰኑ ቡድኖችን ስም እያነሱ ማጠልሸትና መሰል የጥፋት መንገዶችን መራቅ እንደሚገባም አመልክተዋል። " ‘የአማራ መደረጃት ለኢትዮጵያዊነት ስጋት ነው’ የሚሉ አካላት ሚስጥሩ ያልገባቸውና ለውጡን የማይፈልጉ ቡድኖች ናቸው" ያለው ደግሞ ጋዜጠኛና አክቲቪስት ሙሉቀን ተስፋው ነው። ከዚህ ቀደም በማህበራዊ ሚዲያ የአገዛዙን አቅም በማዳከም ለውጥ እንዲመጣ በተደረገው ትግል የሚፈለገው ውጤት መገኘቱን ተናግሯል። "አሁን ላይ ይህን ማድረግ በህዝብ ትግል በጥፋታቸው የተለዩ አካላትን መልሶ የማምጣት እድል የሚሰጥ በመሆኑ አጠቃቀማችን መስተካከል ይገባል" ብሏል። በዚህም በለውጡ የተጎዱ ወገኖች ካሳ እንዲያገኙ፣ አካባቢው ወደ ተረጋጋ ሰላም እንዲመጣና የህግ የበላይነት እንዲከበር ማህበራዊ ሚዲያው በሃላፊነት መስራት እንዳለበት ተናግሯል። በመድረኩም በቀጣይ ማህበራዊ ሚዲያ ምን መምሰል አለበት? የአማራ ብሄርተኝነት እንዴት ይጠናከር? ብአዴን ችግሮችን እንዴት ያርም? በሚሉ ሃሳቦች ላይ ውይይት ተደርጓል። በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት ሆነው ለክልሉ ህዝብ ለውጥ በማህበራዊ ሚዲያ የሚታገሉ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች በምክክር መድረኩ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም