በደሴ ለትምህርት ቤቶች ማቋቋሚያ ድጋፍ ተደረገ

65

ደሴ፤ የካቲት 7/2014 (ኢዜአ) የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በደሴ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ለወደሙና ለተዘረፉ ትምህርት ቤቶች ማቋቋሚያ ድጋፍ እንዲውል አንድ ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና ቁሳቁስን ተበረከተ፡፡
የተበረከተው  ህብረተሰቡን፣ መምህራንና ተማሪዎችን በማስተባበር  እንደሆነ  የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኃይለማሪያም እሸቴ  በርክክቡ ሥነ-ሥነስርዓት ላይ ገልጸዋል።

በዚህም አንድ ሚሊዮን በላይ በጥሬ ገንዝብ እና  በቁሳቁስ ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ሀበት በደሴ ከተማ በሽብር ቡድኑ ለወደሙ ትምህርት ቤቶች ማቋቋሚያ ድጋፍ እንዲውል ይዘው መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከቁሳቁሶቹ  መካከል ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ ጠመኔ፣ የተለያዩ የጽህፈት መሳሪያዎች፣ ደብተርና እስክረቢቶን  ይገኙበታል፡፡

 የሽብር ቡድኑ  የጥፋት ድርጊት የበለጠ አንድነታችን እዲጠናክር፣ እንድንተጋገዝና እንድንተባበር አድርጎናል ያሉት ኃላፊ ፤ በቀጣይም ትምህርት ቤቶች መልሰው እንዲቋቋሙ በሚደረገው ጥረት ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በቡድኑ  የወደሙ ተቋማትን በጋራ መልሶ ማቋቋም ከሁሉም እንደሚጠበቅ ነው ያመለከቱት።

ከባህር ዳር ከተማ የጣና ሃይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  የመጣችው  የዘጠነኛ ከፍል ተማሪ ህሊና ዳኛው  በበኩሏ ''እኛ በምቾት እየተማርን ትምህርት ቤታቸው የወደመባቸው ተማሪዎች መቸገር የለባቸውም'' ብላለች፡፡

ያላቸውን አካፍለው  እንዲማሩ ለማድረግ ተማሪዎችን አስተባብረው የመማሪያ ደብተርና እስክርቢቶ ድጋፍ ማመቻቸታቸውን ጠቁማ፤ አንድነታችንን ለማጠናክርም አግዞናል ነው ያለችው፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሰይድ የሱፍ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈጸመበት ወቅት 80 ትምህርት ቤቶችን በመዝረፉና ያልቻለውን በማውደሙ በትምህርት ዘርፉ ብቻ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡

የወደሙ ትምህርት ቤቶችን በመጠገንና በማስተካከል ትምህርት እንዲጀምሩ ቢደረግም በቁሳቁስ እጥረት በሚፈለገው ልክ ማስተማር እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

መንግስት ህብረተሰቡንና ተቋሞችን በማስተባበር ድጋፍ እያረገ መሆኑን ጠቁመው፤ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር  በተቀናጀ አግባብ ላደረገው ድጋፍም እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

ድጋፉ ወቅታዊ ችግሩን በማቃለል  የመማር ማስተማር ስራውን እንደሚያግዝ አመልክተው፤ ሌሎች ተቋምት፣ ግለሰቦች፣ ባለሃብቶችም መሰል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም