በመዲናዋ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ከተማ አቀፍ የንባብ መርሃ-ግብር ሊካሄድ ነው

67

የካቲት 7/2014/ኢዜአ/ በመዲናዋ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ከተማ አቀፍ የንባብ መርሃ-ግብር እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አስፋው ለገሰ ዛሬ በሰጡት መግለጫ መርሃ ግብሩ በከተማ ደረጃ ሲካሄድ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ነው፡፡

መርሃ ግብሩ ”ንባብ ለሰላም እና ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ”በሚል መሪ ሃሳብ ከየካቲት 9 እስከ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በቅርቡ በተመረቀው በአብርሆት ቤተ መፅሐፍት እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

የመርሃ-ግብሩ ዋነኛ ዓላማ በመዲናዋ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንባብ ባህል ማጎልበት መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

መርሃ-ግብሩ ደራሲዎች ስራዎቻቸውን ለአንባቢያን ተደራሽ እንዲያደርጉ እድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፤ በተለይ በከተማዋ በሚገኙ የህዝብ ቤተ-መጽሐፍትና መፅሀፍት ሻጮች መካከል ጠንካራ ትስስር ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡

በመርሃ ግብሩም 48  የሚሆኑ የተለያዩ ተቋማት ተሳታፊዎች ሲሆኑ፤ ከእነዚህም መካከል 22ቱ መጽሃፍ የሚሸጡ ድርጅቶች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ህብረተሰቡ በአብርሆት ቤተ መፅሀፍት በመገኘት የመርሃ-ግብሩ ተሳታፊ እንዲሆንም ምክትል ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም