ባንኩ አሰራሩን በማዘመን ለዓለም አቀፍ ውድድር መዘጋጀት ይጠበቅበታል

56

የካቲት 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰራሩን በማዘመን ለዓለም አቀፍ ውድድር መዘጋጀት ይጠበቅበታል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስገነባውን ባለ 53 ወለል የዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ታሪክ ውስጥ ደምቆ የሚታይ አንጋፋ ተቋም መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ባንኩ ባሉት ቅርንጫፎች ብዛትና በሚሰጠው አገልግሎት በአገር ውስጥ ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገቡን አስታውሰው፤ ነገር ግን ይህንን ስኬት ወደ ቀጠናው ብሎም ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ማስፋት ይገባል ነው ያሉት፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየጊዜው እየዘመኑ እና በፍጥነት እየተለዋወጡ ከሚገኙ ዘርፎች አንዱ የባንክ ሴክተር መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ዘርፉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ይዞት የሚመጣውን የውድድር አውድ በር በመዝጋት መከላከል አይቻልም ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰራሩን በማዘመን በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ ለመሆን መዘጋጀት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ባንኮች የሰፊው ህዝብ ሃብት በመሆናቸው የብድር ስርዓታቸው አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአገር አቀፍ ደረጃ በ1 ሺህ 795 ቅርንጫፎችና 66 ሺህ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን፤ አጠቃላይ ሃብቱም 1 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም