የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዋርካ ነው

148

የካቲት 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዋርካ ነው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስገነባውን ባለ 53 ወለል አዲስ የዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ መርቀው ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ የፋይናንሰ ዋርካ ነው ብለዋል።

ለዚህም ደግሞ ባንኩ በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ባንኮች ካላቸው ተቀማጭ ሃብት ከ52 በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪ ባንኩ በአገሪቱ በዘርፉ ካለው አጠቃላይ ሃብት ውስጥ ከ62 በመቶ በላይ የሚሆነውን መያዙም ባንኩን የፋይናንስ ዋርካ ያሰኘዋል ነው ያሉት።

አሁን ላይ ከአንድ ትሪሊየን ብር በላይ ሃብት ያለው ባንክ መሆኑም ሌላኛው የዋርካነቱ መገለጫ መሆኑን አንስተዋል።

በሌላ በኩል ባንኩ ኢትዮጵያ ተቋማትን በመገንባት ለትውልድ ማሸጋገር እንደምትችል ህያው ምስክር መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ታሪክ የፋይናንስ መዝገበ ቃላት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባንኩ የማያልቅ እውቀት ባለቤት መሆኑንም መስክረዋል።

"የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዩኒቨርስቲ" ሲሉ ባንኩ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላለፉት 80 ዓመታት ለደንበኞች ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ሲሰጥ ቆይቷል።በተለይም በፋይናንስ እና በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንዲሁም በወጪ፣ ገቢ እና በአገር ውስጥ ንግድ ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ሲያበረክት እንደቆየም ይታወቃል።

ባንኩ ዛሬ ያስመረቀው ህንጻ 209 ነጥብ 15 ሜትር ከመሬት በላይ ከፍታ እና 65 ሺህ ስኩየር ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፤ በውስጡም እስከ 1 ሺህ 500 መኪና ማቆም የሚችል ዘመናዊ ፓርኪንግ፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ ሙዚየም፣ ሲኒማ ቤት እና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ክፍሎችን ይዟል፡፡

ለግንባታውም 303 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም