የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአገር ልማትና እድገት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ይቀጥላል

59

የካቲት 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአገር ልማትና እድገት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አዲሱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ መርቀው ከፍተዋል፡፡

ህንጻው ከመሬት በላይ 209 ነጥብ 15 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን፤ ከመሬት በታች ያሉትን ጨምሮ 53 ወለል አለው፡፡

በውስጡ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ሙዚየም ፣ሲኒማ ቤት እና እስከ 1 ሺህ 500 መኪናዎችን ማቆም የሚችል  ቦታ አለው፡፡

የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በዚህን ወቅት ህንጻው የአዲሱን ትውልድ የባንክ አገልግሎት አሰጣጥን የተከተሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንደተገጠሙለት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአገር ኢኮኖሚ እንዲጎለብት የበኩሉን ኃላፊነት ሲወጣ መቆየቱን አስታውሰው፤ ይህንኑን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በአገሪቷ የሚገኙ የተለያዩ የግል ባንኮች እንዲቋቋሙ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድም ለህልውና ጦርነት፣ ለገበታ ለአገር፣ ለህዳሴ ግድብና እና ሌሎች ኀብረተሰቡን የሚጠቅሙ ደጋፎችን ማከናወኑንም አንስተዋል፡፡

አዲሱ የባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ተጠናቆ ወደ ስራ መግባት ደግሞ ለባንኩ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርለት ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ለህንጻ ግንባታው በስኬት እንዲጠናቀቅ ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም