የ"በቃ" ወይም ‘#NoMore’ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያንና ምስራቅ አፍሪካን ለመጉዳት የተዘጋጀውን 'ኤችአር 6600' ረቂቅ ሕግ አወገዘ

82

የካቲት 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) የ"በቃ" ወይም #NoMore ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያንና ምስራቅ አፍሪካን ለመጉዳት የተዘጋጀውን 'ኤችአር 6600' ረቂቅ ሕግ አወገዘ።

እንቅስቃሴው አሜሪካ ካሉ አጋሮቹ ጋር በመሆን ረቂቅ ሕጉን ስፖንሰር ባደረጉት የዴሞክራትና የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት በምርጫ ድምጽ በመንፈግ ከአባልነታቸው እንዲወርዱ እሰከ ማድረግ የሚደርስ እንቅስቃሴ አደርጋለሁ ብሏል።

በአሜሪካ የኮንግረስ አባላት ቶም ማሊኖውስኪ (ኒው ጀርሲ)፣ ያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ዴቪድ ሲሲሊን(ሮድ አይላንድስ)ና ብራድ ሼርማን(ካሊፎርኒያ) ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) 'ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት' ወይም ኤችአር 6600 በሚል ያዘጋጁት ረቂቅ ሕግ ከሰሞኑ በኮንግረሱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት እንደተደረገበት ይታወቃል።

የ"በቃ' ወይም #NoMore ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያንና ምስራቅ አፍሪካን ለመጉዳት የተዘጋጀ ነው ያለውን 'ኤችአር 6600' ረቂቅ ሕግ በጽኑ እንደሚያወግዝ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ሕጉ በኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስትና ሕዝቦች ላይ አሉታዊ ጉዳት የማድረስ ውጥን ያለውና አፍራሽ አካሄድን የተከተለ መሆኑን ገልጿል።

በተለይም ረቂቅ ሕጉ አሜሪካ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ የልማት እርዳታ መከልከልና ማዕቀቦች እንድትጥል የቀረበው ሀሳብ ሃላፊነት የጎደለውና ተቀባይነት የሌለው እንደሆነም ነው እንቅስቃሴው የገለጸው።

በ’አሜሪካ የሆምላንድ ሴኩዩሪቲ’ ደረጃ 3 የሽብርተኛ ተቋም ተብሎ የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት እንዲጀመር መድረጉንና ወደ ኤርትራም ሚሳኤል በመተኮስ ትንኮሳ ሲፈጽም የነበረ ቢሆንም የባይደን አስተዳደርና የ'ኤች አር 6600' ስፖንሰሮች ይሄን እውነታ ሊረዱት አልፈለጉም ብሏል።

'ኤችአር 6600' “በኢትዮጵያ ሰላም፣ መረጋትትና ዴሞክራሲን አመጣለሁ” በሚል ሽፋን እኩይና አፍራሽ አለማን ለማስፈጸም መዘጋጀቱን አመልክቷል።

የ"በቃ" ወይም ‘#NoMore’ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ የኤችአር 6600 ስፖንሰሮችና የባይደን አስተዳደርን የሚቃወም ዘመቻ በማህበራዊ ትስስር ገጽ አማራጮች መጀመሩን አስታውቋል።

እንቅስቃሴው አሜሪካ ካሉ አጋሮቹ ጋር በመሆን ረቂቅ ሕጉን ስፖንሰር ባደረጉት የዴሞክራትና የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት በምርጫ ድምጽ በመንፈግ ከአባልነታቸው እንዲወርዱ እሰከ ማድረግ የሚደርስ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግም አስገንዝቧል።

አንዳንድ የአሜሪካ ባለስልጣናት በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚከተሉትን አፍራሽ አካሄድ በማቆም አገራት ከአሜሪካ ጋር በጋራ ጥቅምና መከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖራቸው ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮ-አሜሪካውያን የእድገት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት፣ ’አሜሪካን ኢትዮጵያንስ ፐብሊክ አፊሪስ ኮሚቴና ሌሎች በአሜሪካ የሚገኙ የሲቪክ ተቋማት የ 'ኤችአር 6600' ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ዘመቻ መጀመራቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም