የአጥንት ካንሰር ታማሚ ነኝ በሚል በሀሰት የህክምና ማስረጃ ስትለምን የቆየችው ወጣት በቁጥጥር ስር ዋለች

111

ጭሮ፤የካቲት 4/2014(ኢዜአ) የአጥንት ካንሰር ታማሚ በመምሰል በተሽከርካሪ እየተዘዋወረች ስትለምን የነበረችውን ወጣት ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጭሮ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ወጣቷ ከሰባት ግብረ አበሮቿ ጋር የአጥንት ካንሰር ታማሚ መስላ በተለያዩ ከተሞች እየተዘዋወረች  ስትለምን መቆየቷን በምርመራ ማረጋገጡን ፖሊስ ገልጿል።

የጭሮ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጂን ካሳሁን ባይሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ወጣቷ ግብረ አበሮቿ ጋር በሀሰት የህክምና ማስረጃ የእርዳታ ጥሪ እያሉ ህብረተሰቡን ሲያጭበረብሩ እንደነበረም የፖሊስ  ምርመራ ያሳያል።

ዋና ሳጂን ካሳሁን እንዳሉት ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ  በተከራዩት መኝታ ቤት ውስጥ 24ሺህ 260 ብር በመቁጠር ላይ እንዳሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።

የአጥንት ካንሰር ታማሚ መስላ በመተወን ህብረተሰቡን በማጭበርበር ገንዘብ ትለምን የነበረችው ወጣት ከነግብረ አበሮቿ በህግ ቁጥጥር ስር መዋሏን ዋና ሳጂን ካሳሁን ተናግረዋል፡፡

ወጧቷ ለፖሊስ በሰጠችው ቃል በጭሮ ከተማ ላለፉት 15 ቀናት በፎቶግራፏና የካንሰር ታማሚ መሆኗን በሚገልፅ ጽሁፍ በያዘ ባነር በተሸፈነ ሚኒባስ መኪና እየተዘዋወረች ስትለምን መቆየቷን ገልፃለች ብለዋል።

ወጣቷ 1ሺህ 500 ብር በቀን እየከፈለቻት ታማሚ መስላ እንድትለምን በቀጠረቻት ሴት ምክር ተታላ የማጭበርበር ድርጊቱን  እንደጀመረች ለፖሊስ ማስረዳቷን ዋና ሳጂን ካሳሁን ገልጸዋል።

የማጭበርበር ድርጊቱን መናገርና መንቀሳቀስ እንደማትችል ሆና በሰዎች ተደግፋ ህዝብን በሀዘኔታ ሰዎችን እያራራች ትፈጽም እንደነበርና የሰበሰበችውን በርካታ ገንዘብ ለቀጠረቻት ግለሰብ ትሰጥ እንደረነበር ገልጻለች ብለዋል።

የቀጠረቻት ግለሰብም የተመደበላት ገንዘብ 1ሺህ 500 ብር ብቻ እየተሰጠቻት ትነግድባት እንደነበርም ለፖሊስ አስረድታለች።

የድርጊቱ አቀነባባሪና የሀሰት የህክምና ማስረጃውን አስይዛ መለመኛ ያደረገቻት ወጣት ደግሞ በአዲስ አበባ አውቶቡስ ተራ አካባቢ ሻይ ቡና በመስራት ትተዳደር የነበረች መሆኗንም አመላክታለች።

ወጣቷ ለፖሊስ በሰጠችው የእምነት ቃል በመስተንግዶ ስራ ላይ ተሰማርታ ከነበረችና አሁን ግብረ አበሯ ከሆነች ጓደኛዋ ጋር በመመካከር በአቋራጭ ለመክበር አስባ ድርጊቱን እንደጀመረችው ትናገራለች።

የህክምና ማስረጃውም በቅርቡ በአጥንት ካንሰር በሽታ የሞቱት እናቷ መሆኑን ተናግራ መነሻቸው ከአዲስ አበባ መሆኑንና ከአራት ወራት በፊት በስምምነት ስራውን እንደጀመሩትም አስረድታለች።

የማጭበርበር ድርጊቱን ጭሮን ጨምሮ በጅማ፣ ቢሾፍቱ፣ አዳማ፣ ሀረር፣ ድሬደዋ፣ በዴሳ፣ መተሃራ፣ ወልቂጤና ሌሎች ከተሞች እየተዘዋወረች ስትፈጽም መቆየቷን ተናግራለች።

ወጣቷ የማጭበርበር ድርጊቱን ከፈጸመችባቸው የከተሞች አስተዳደሮች ፈቃድ ያገኘች የሚያስመስል ሀሰተኛ ደብዳቤ በመያዝ እንደሆነም አስረድታለች ፡፡

ወጣቷ ለሰባቱ ግብረ አበሮቿ በቀን ለእያንዳንዳቸው 1ሺህ 500 ብር ትከፍል እንደነበርና ለተከራየችው ሚኒባስ መኪና ደግሞ በተመሳሳይ 5ሺህ ብር ወደ አዲስ አበባ እንደምትልክ በሰጠችው የእምነት ቃል ማረጋገጧን ዋና ሳጂን ካሳሁን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም