ፋውንዴሽኑ በ4 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ዘመናዊ የእህል ወፍጮዎችን ለምዕራብ ኦሞ ከፊል አርብቶ አደሮች አስተከለ

215

ሚዛን፤ የካቲት 05/2014 (ኢዜአ)፡የሃይለ ማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን 4 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አምስት የእህል ወፍጮዎችን በምዕራብ ኦሞ ዞን ለሚገኙ ከፊል አርብቶ አደሮች አስተከለ።
ፋውንዴሽኑ   ወፍጮዎችን ያስተከለው በዞኑ በመኤኒት ጎልዲያ እና በመኤኒት ሻሻ ወረዳዎች ውሰጥ ነው።

በእህል ወፍጮዎቹ ርክክብ ሥነ ሥርዓት ትናንት በሁለቱ ወረዳዎች በተካሄደበት ወቅት የፋውንዴሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ እንዳሉት የእህል ወፍጮዎቹ በሥርዓት ከተያዙ ለረጅም ዓመታት የማገልገል አቅም አላቸው።

"የወፍጮዎቹ መተከል በአካባቢው  የሚገኙ  ሴቶችን  የእለት  ተእለት ድካም  በማቃለል ጊዜያቸውን ለሌሎች የልማት ስራዎች በማዋል ምርታማ እንዲሆኑ ያግዛል" ብለዋል።

ፋውንዴሽኑ ቀደም ሲል  በአካባቢው ባካሄደው ጥናት በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሳቢያ ሴቶች ለከፍተኛ የስራ ጫና እንደሚዳረጉ  ማረጋገጡን ገልጸዋል።

ልጅ ከማሳደግ ባለፈ ከሩቅ ቦታ እንጨት መስበር፣ ውሃ በመቅዳትና እህል በድንጋይ መፍጨት የዘወትር ተግባራቸው መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን የስራ ጫና ለማቃለል እና በአካባቢው  ማህበረሰብ  ዘንድ  መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ መንግስት እና የግሉ ባለሀብት ትኩረት ሰጥተው እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

በተለይ የህብረተሰቡ ኢኮኖሚያወና ማኅበራዊ ኑሮ  እንዲሻሻል  ለትምህርት ዘርፉ ቅድሚያ ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በመኤኒት ጎልዲያ ወረዳ የኩሻንታ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሻርያ ካራ በአከባቢያቸው ወፍጮ ባለመኖሩ  እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው ሴቶች  እህልን በድንጋይ ሲፈጩ ቆይተዋል።

ከ''ድካማችንና ከችግራችን እፎይታን የሚሰጠን ወፍጮ በደጃችን በመምጣቱ ተደስተናል'' ያሉት ወይዘሮ ሻርያ ለፋውንዴሽኑ ምስጋና አቅርበዋል።

 "ለገንፎና ለሌላም ምግብነት የሚያገለግሉ  የእህል ምርቶችን ብናመርትም ወፍጮ በቅርብ ስለሌለ በቀላሉ ምግብ አዘጋጀተን ለመጠቀም እንቸገር ነበር" ያሉት ደግሞ  የቀበሌው ነዋሪ ከፊል አርብቶ አደር  ወይዘሮ ካያ ቦኒ ናቸው።

የመኤኒት ጎልዲያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ እግለች በፋውንዴሽኑ የተደረገው አስተዋጽኦ የአካባቢውን ሴቶች  ችግር የሚፈታ መሆኑን ተናግረዋል።

የእህል ወፍጮ ፍለጋ ከተማ በመሄድ ለመዋልና ለማድር ይገደዱ ለነበሩ ከፊል አርብቶ አደሮች እፎይታን እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ፋውንዴሽኑ በምዕራብ ኦሞ ዞን የመኤኒት ጎልዲያ እና መኤኒት ሻሻ ወረዳዎች የእህል ወፍጮ ድጋፍ በተጨማሪ ለ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  ልጃገረድ ተማሪዎች 325 ሺህ ብር ወጭ በማድረግ የተለያዩ አጋዥ መጽሐፍት እና ከአንድ ዓመት በላይ እየታጠበ ማገልገል የሚችል የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ ማድረጉ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም