የአካል ጉዳተኛ ማህበራትን አቅም ለማጎልበት ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ስራ ተገብቷል

194

ሀዋሳ፤ የካቲት 05/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን የአካል ጉዳተኛ ማህበራትን አቅም ለማጎልበት ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ስራ መገባቱን አስታወቀ።

ፌዴሬሽኑ በሲዳማና ደቡብ ክልል ለሚገኙ አካል ጉዳተኛ ማህበራት የተለያዩ የቢሮ ቁሳቁሶችን ዛሬ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት፤ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን በሀገሪቱ ያሉ የአካል ጉዳተኛ ማህበራትን አቅም ለማጎልበት ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ በሰባት ክልሎች 5 ሚሊየን በሚሆን ወጪ የቢሮ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ለሲዳማና ደቡብ ክልሎች ዛሬ የተደረገው ድጋፍ የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸው፤ ከ900 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ ቁሳቁሶችን  ማበርከቱን አመልክተዋል።

ፌዴሬሽኑ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ባደረገው ተቋማዊ ለውጥ ክልሎችን አባል አድርጎ መንቀሳቀስ መጀመሩን ያወሱት ዳይሬክተሩ፤ማህበራቱን የመደገፉ  ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

ክልሉ አዲስ መሆኑን ተከትሎ አዳዲስ የአካል ጉዳተኛ ማህበራት መቋቋማቸውን የተናገሩት ደግሞ የሲዳማ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ በቀለ ናቸው፡፡

በክልሉ በየጉዳቱ ዓይነት የተደራጁ ማህበራትን ለማጠናከር የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን  ጠቅሰዋል።

ዛሬ የተረከቧቸው የቢሮ ቁሳቁሶች ማህበራቱን በማጠናከር ለአባላቶቻቸው የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያግዝ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፕሬዚዳንት አቶ ሁሴን ሁቃቶ በበኩላቸው፤ ፌዴሬሽኑ 400 ሺህ ብር በሚጠጋ ገንዘብ ወጪ ያደረገበትን የቢሮ ቁሳቁስ ድጋፍ በአርባምንጭና ወላይታ ዞን ለሚገኙ ሰባት ማህበራት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

አብዛኞቹ ማህበራት የቢሮ ቁሳቁስ ያልተሟላላቸው በመሆናቸው ከኪሳቸው ገንዘብ እያወጡ ፎቶ ኮፒና የጽሁፍ ስራዎችን እንደሚያከናውኑ ጠቅሰው፤ የተደረገው ድጋፍ ይህንን ችግር እንደሚፈታ ተናግረዋል።

ኮምፒዩተር፣ ፕሪንተር ፣ ፎቶ ኮፒ ማሽን የቢሮ ወንበሮችና ለአይነሰ ስውራን የሚሆኑ መለማመጃ ኮሚፒዩሮችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች የተደረጉ ሲሆን በድጋፍ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሁለቱ ክልሎች ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉ የአካል ጉዳተኞች ውስጥ 95 ከመቶ የሚሆኑት ከድህነት ወለል በታች መሆናቸውን በቅርቡ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያመላክታል።

በ1989 የተመሰረተው የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን በስሩ ከ22 በላይ ማህበራት እንዳሉት ከፌዴሬሸኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም