የጋምቤላ ከተማ የመሰረተ ልማት ችግሮች ለማቃለል ማህበረሰቡ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ተጠየቀ

155

ጋምቤላ፣ የካቲት 5/2014 (ኢዜአ) የጋምቤላ ከተማን የመሰረተ ልማት ችግሮች ለማቃለልና እድገቷን ለማፋጠን በሚከናወኑ ሥራዎች ማህበረሰቡ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ።

በጋምቤላ ከተማ በህዝቡና በመንግስት ተሳትፎ ከ69 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባ ሁለት ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ዛሬ ተመርቋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ መንገዱን በመረቁበት ወቅት እንዳሉት የጋምቤላ ከተማ የ100 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ብትሆንም የዕድሜዋን ያህል እድገት ሳታሳይ ቆይታለች።

ለከተማዋ እድገት መጓተት ቀደም ሲል የነበሩ ብልሹ አሰራሮችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተጠቃሽ ምክንያት መሆናቸውን አመልክተዋል።  

በከተማው የሚስተዋለው የመሰረተ ልማት ችግር ለከተማዋ እድገት ከፍተኛ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት መንግስት የከተሞችን መሰረተ ልማት ለማሻሻልና እድገታቸውን ለማፋጠን ለጀመራቸው ሥራዎች ስኬት የህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በተለይ በጋምቤላ ከተማ ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ የከተማውን የውስጥ ለውስጥ መንገድ ለማሻሻል እየተደረገ ባለው ጥረት የከተማዋ ህዝብ እያሳየ ላለው ተሳትፎ ርዕሰ መስተዳድሩ አመስግነው፣ በቀጣይም ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

በህዝብና በመንግስት ተሳትፎ ተገንብቶ ዛሬ የተመረቀው የሁለት ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ለህዝቡ ተሳትፎ ጥሩ ማሳያ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተንኳይ ጆክ በበኩላቸው የጋምቤላ ከተማ ከተቆረቆረች ረጅም ዕድሜ እንዳላት ተናግረዋል።

ይሁንና ባለፉት ዓመታት ትኩረት ተነፍጓት በመቆየቷ የመሰረተ ልማት ችግሩ በየጊዜው እየሰፋ መምጣቱን ገልጸዋል።

በተለይም የከተማዋ ህዝብ ቁጥር እያደገ መምጣት ለህብረተሰቡ መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ ማድረጉን  ኃላፊው ጠቁመዋል።

በከተማዋ የሚታየውን የመሰረተ ልማት ችግር ለማቃለል በሚከናወኑ ተግባራት የህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ከተገኙት የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አባንግ ኡጃቶ በሰጡት አስተያየት፣ የተመረቀው መንገድ ቀደም ሲል በብልሽት ምክንያት ለመኪናም ሆነ ለእግረኛ ያስቸግር እንደነበር አስታውሰዋል።

መንገዱ በአዲስ መልክ ተገንብቶ ለምረቃ በመብቃቱ የህዝቡና የአሽከርካሪዎች ችግር መፍታቱን ተናግረዋል።

በጋምቤላ ከተማ ከፍተኛ ብልሽት ከነበረባቸው የውስጥ ለውስጥ መንገዶች መካከል አንዱ በእለቱ የተመረቀው የአስፓልት መንገድ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ አቶ አብዱ አቡበከር ናቸው።

አቶ አብዱ እንዳሉት መንገዱ ከመበላሸቱ ባለፈ የውሃ መውረጃ ሆኖ ስለነበር ህዝቡን ለችግር ዳርጎት ቆይቷል።

በዛሬው እለት መንገዱ ተገንብቶ ችግሩ በመፈታቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም