አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል ጥቃት በመፈፀም በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሰና ወደ ትግራይ ክልልም ሰብአዊ እርዳታ እንዳይገባ መተላለፊያ ዘግቷል

148

የካቲት 5/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል ጥቃት በመፈፀም በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰና ወደ ትግራይ ክልልም ሰብአዊ እርዳታ እንዳይገባ የመተላለፊያ ኮሪደር መዝጋቱን መንግስት አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ተቀማጭነታቸውን ላደረጉ የተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የመከላከያ ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረበቴ አገራትና የኢጋድ  ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል፤ የሽብር ቡድኑ ከዚህ ቀደም በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በሰዎች፣ በንብረትና በመሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ የጥፋት እንቅስቃሴ አሁንም በመቀጠሉ በአፋር ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ወረራ ፈፅሞ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ መሆኑን አስረድተዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ወደ ትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ እንዳይገባ የመተላለፊያ ኮሪደር በመዝጋቱ መንግስት በአውሮፕላን ሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ይገኛልም ብለዋል።

አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት "ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እየደረሰ አይደለም" በሚል የተሳሳተ ምልከታ መንግስትን እየወቀሱ የሽብር ቡድኑን ትንኮሳ በዝምታ እየተመለከቱት ነው ብለዋል።

በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ቡልቲ ታደሰ፤ ሰራዊቱ ባለበት ፀንቶ እንዲቆም የተላለፈውን ትዕዛዝ ተከትሎ አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል ዳግም ወረራና ጥቃት እየፈፀመ መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት በጥፋት እንቅስቃሴው ቀጥሎ በአፋር ክልል ወረራ በመፈፀም በዜጎች ላይ ከፍተኛ ግፍና በደል እየፈፀመ መሆኑን ጠቅሰው ወደ ትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ እንዳይገባም የመተላለፊያ ኮሪደር ዘግቷል ብለዋል።

እየተፈጠረ ላለው ቀውስ ምክንያት የሆነው አሸባሪው ህወሃት መሆኑን በማስረዳት መንግስት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆኑንም አብራርተዋል።

አሸባሪው ህወሃት ይዞት የነበረውን አገር የማፍረስ እቅድ በማክሸፍ ኢትዮጵያዊያን ህልውናቸውን አስጠብቀዋል ብለዋል ብርጋዴር ጀኔራል ቡልቲ በማብራሪያቸው።

የመጀመሪያውን ህብረ ብሄራዊ ዘመቻ በድል ተጠናቆ መንግስት ወደ መደበኛ ስራው ቢገባም የሽብር ቡድኑ አሁንም ከጥፋት ተግባሩ ሊቆጠብ አለመቻሉንም አስረድተዋል።

በመሆኑም የአገር መከላከያ ሰራዊት አገርን ከጥፋት ለመታደግ ሲል በአሸባሪው ላይ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎች ማብራሪያ ከተሰጣቸው በኋላ የአገር መከላከያ ሚኒስቴርን ዋና መሥሪያ ቤት ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም