የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሀገራቸውን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ

178

ጋምቤላ፣ የካቲት 5/2014(ኢዜአ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች የሀገራቸውን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ።

የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ህብረት 41ኛ መደበኛ ጉባኤ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ፒተር አማን በህብረቱ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች የሀገሪቱን ሰላምና እንድነት በማስጠበቅ ረገድ  የላቀ ኃላፊነት አለባቸው።

"የከፍተኛ ትምህርት የሁሉም ክልል ወጣቶች መገኛ በመሆኑ ሰላምና አንድነትን በማስጠበቅ ረገድ ለህብረቱ የበለጠ ምቹ አጋጣሚ ያለው ነው" ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ለህዝቦች አንድነት መከበር ከትምህርት ተቋማቱ ጀምሮ በየሚመለሱባቸው አካባቢዎች ሁሉ የዜግነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አቶ ፒተር አሳስበዋል።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ከተማ ጥላሁን " በበኩላቸው የተማሪዎች ህብረት የተማሪዎችን መብትና ጥቅም ከማስከበር ባለፈ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን አስተማማኝ በማድረግ ጭምር አስተዋፆቸው የላቀ ነው" ብለዋል።

በቀጣይም ያላቸውን ተሞክሮ እና አቅም በመጠቀም ከትምህርት ተቋማት ባለፈ ለኢትዮጵያ ሰላም አንድነትና እድገት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ጉባኤው የህብረቱን የቀጣይ ስራዎች ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ እንደሚመክር እምነታቸውን ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሀገር አቀፍ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ ኦሊ በዳኔ በዚሁ ጊዜ እንዳለው በ1970ዎቹ አካባቢ የተመሰረተው የተማሪዎች ህብረት በሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንቅስቃሴ ሲያደርግ የቆየ ረጅም ታሪካዊ ዳራ ያለው ነው።

አሁን ላይም ህብረቱ በሀገሪቱ ወቅታዊና ሌሎች ጉዳዮች በመምከርና በማስተባበር ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረቱ እንደ ሀገር የተፈጠሩ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ፣ የኮቪድ ወረርሽኝና ሌሎች ተጽኖዎችን በመቋቋም የመማር ማስተማር ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን የድርሻውን ሲያበረክት ቆይቷል ብለዋል።

በጋምቤላ ከተማ ትናንት ምሽት የተጀመረው የህብረቱ ጉባኤ ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን በቆይታው የህብረቱን አመራር ምርጫ እንደሚያካሂድ ይጠበቃል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም