የመላ ጋምቤላ ዓመታዊ የስፖርት ውድድር ተጀመረ

57

የካቲት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዘጠነኛው የመላ ጋምቤላ ዓመታዊ የወረዳዎች የስፖርት ውድድር በጋምቤላ ወረዳ አቦል ከተማ ዛሬ በይፋ ተጀመረ።

በስፖርት ውድድሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ውድድሩን ያስጀመሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በወቅቱ እንዳሉት፤ ስፖርት የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ረገድ የጎላ ፋይዳ ስላለው ውድድሩን በጨዋነት ማካሄድ ይገባል።

በመሆኑም ውድድሩ አንድነትን በሚጠናክር መልኩ ፍፃሜውን እንዲያገኝ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ውድድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ለመምርጥና ለማብቃት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ታይዶር ቻንባንግ ክልሉ የሚወክሉ ምርጥ ስፖርተኞችን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ የተጀመረው ዘጠነኛው የመላ ጋምቤላ ዓመታዊ የወረዳዎች ስፖርት ውድድር የጥረቱ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

በጋምቤላ ወረዳ አዘጋጅነት ከዛሬ የካቲት 5 ቀን 2014 ጀምሮ ለ20 ቀናት በሚቆየው ውድድር ጋምቤላ ከተማ አስተዳድርን ጨምሮ 14 ወረዳዎች በእግር ኳስ፣ በመረብ ኳስ፣ በቅርጫት ኳስ፣ በአትሌቲክስና ሌሎች የስፖርት ዓይነቶች እንደሚሳተፉ ከድርጊት መርሃ ግብሩ ለማወቅ ተችሏል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም