የማንጎ በሽታን የሚያስወግዱ ነፍሳትን ከደቡብ አፍሪካ ለማስመጣት ጥረት እየተደረገ ነው

103

አሶሳ ፤ የካቲት 05 /2014 (ኢዜአ) የማንጎ በሽታ አምጪ ተባዮችን በመመገብ በሽታውን የሚያስወግዱ ነፍሳትን ከደቡብ አፍሪካ ለማስመጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።

በማዕከሉ የእጽዋት ጥበቃ የሥራ ሂደት ተቆጣጣሪ እና የሰብል በሽታ ተመራማሪ አቶ ምንያህል ከበደ እንደገለጹት

ነፍሳቶቹ ውጤታማነታቸው በሙከራ የተረጋገጠ ሲሆኑ የጎንዮች ጉዳትም የላቸውም።

የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋው መልካሙ ፤በአሶሳና አካባቢው "ኋይት ስኬል" የተባለ የማንጎ ተባይ በሽታ ከዓመታት በፊት መከሰቱን አስታውሰዋል።

ማዕከሉ አዳዲስ የተሻሻሉ የማንጎ ዝርያዎችን ከውጭ በማስመጣት የማንጎ ተባይ በሽታ ጉዳት በመቀነስ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለመመለስ ማዕከሉ ለዓመታት ምርምር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ምርምሩ አራት አዳዲስ የተሻሻሉ የማንጎ ዝርያዎችን ከውጭ በማስመጣት ማላመድን ያካተተ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አዲስ የማንጎ ዝርያዎችን የማላመዱ ሥራ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በሙከራ ደረጃ መጀመሩን፣ አመልክተው፤ በቅርቡ ለአብዛኞቹ አርሶ አደሮች የማድረስ ስራ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

አቶ ተስፋው እንዳሉት፤ አዳዲሶቹ ዝርያዎች ለፋብሪካዎች የጁስ ምርት በግብአትነት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የሰብል ልማት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ንጉሴ አሻግሬ በበኩላቸው፤ የማንጎ በሽታ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ መከሰቱን አስታውሰዋል።

ችግሩ ከተከሰተ ጀምሮ ቢሮው ከአሶሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር ተቀናጅቶ በምርምር እና በባህላዊ መንገድ መፍትሄ ለማምጣት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

ሞዴል አርሶ አደሮችን ማዕከል በማድረግ የማንጎ በሽታ የሚያስከትለውን ጉዳት በማስገንዘብ በሽታውን እንዲከላከሉ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም አቶ ንጉሴ ገልጸዋል።

በአንድ ሄክታር መሬት ከ200 በላይ የማንጎ ዛፎች የሚገኙ ሲሆን ከአንድ የማንጎ ዛፍም እስከ ሁለት ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ታውቋል።

በክልሉ በየዓመቱ ከየካቲት እስከ ሚያዚያ ወራት ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ኩንታል ማንጎ ቢመረትም በበሽታው ምክንያት ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው እንደሚባክን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም