በሃገሪቱ ላይ የሚደርሱ ውጫዊ ጫናዎችን ከመመከት ባሻገር በብሄራዊ ደረጃ ዘላቂ ሰላም እና ዕድገትን ለማረጋገጥ መደገፍይገባል

58

የካቲት 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሃገሪቱ ላይ የሚደርሱ ውጫዊ ጫናዎችን በአንድነት ከመመከት ባሻገር በብሄራዊ ደረጃ የተጀመረውን ዘላቂ ሰላም እና ዕድገት የማረጋገጥ ጥረት በህብረት መደገፍ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

አቶ ደመቀ፤ የ"በቃ" ዓለምአቀፍ ንቅናቄን በማስተባበር በሰሜን አሜሪካ ከሚንቀሳቀሰው "የሰላምና አንድነት ግብረሃይል" አመራሮች እና አባላትን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ ላይ የውጪ ሃይሎች ሃገር ውስጥ ካሉ የጥፋት ቡድኖች ጋር ጥምረት በመፍጠር ኢትዮጵያን ለማፍረስ በተለያዩ ግንባሮች የከፋ ጥፋት በመፈፀም እና የከረረ ጫና በመፍጠር የሃገርን ሉዓላዊነትን ሲፈታተኑ እንደነበር አቶ ደመቀ አስታውሰዋል።

በተለይ በውጪ ሃይሎች የሚወሰዱት ፍትሃዊነት የጎደላቸው እርምጃዎች የሃገሪቱን ሉዓላዊነት በእጅጉ እንደተፈታተኑ በመጥቀስ፤ ውጫዊ ጫናዎችን የመመከት ተልዕኮ ራሱን የቻለ ፈታኝ ግንባር እንደነበር አቶ ደመቀ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ደመቀ ገለፃ ውጫዊ ጫናዎች በሚመከቱበት ግንባር በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በ"በቃ" የንቅናቄ መርህ በዓለም አደባባይ ለሃገራቸው ፍትህን በመሻት ድምፃቸውን በስፋት አስተጋብተዋል።

በተመሳሳይ በሰሜን አሜሪካ የ"በቃ" ንቅናቄን በማስተባበር እና በመምራት "የሰላምና አንድነት ግብረሃይል" አመራሮች እና አባላት የዚህ ታሪካዊ ዘመቻ አካል በመሆን ላበረከቱት አስተዋፅዖ አቶ ደመቀ አመስግነዋል።

በሁሉም ግንባሮች ኢትዮጵያዊ አንድነትን ጠብቆ እና አጥብቆ መጓዝ ተደማጭነትን ከማረጋገጡ ባሻገር ትርጉም አዘል ድሎችን ለማስመዝገብ እንደሚያግዝ ከዓለምአቀፍ ንቅናቄው ቋሚ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል ብለዋል አቶ ደመቀ።

በሃገር አቀፍ ደረጃ መንግስት ዘላቂ ሰላም እና ዕድገት ለማረጋገጥ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ ደመቀ በዝርዝር አብራርተዋል።

በመጨረሻም በሃገሪቱ ላይ የሚደርሱ ውጫዊ ጫናዎችን በአንድነት ከመመከት ባሻገር በብሄራዊ ደረጃ የተጀመረውን ዘላቂ ሰላም እና ዕድገት የማረጋገጥ ጥረት በህብረት መደገፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም