መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን መቀበል ጀመረ

692

ደሴ፤ የካቲት3/2014 በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ውድመትና ዘረፋ የደረሰበት መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ መልሶ ተደራጅቶ በመጀመሪያው ዙር ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መቀበል መጀመሩን አስታወቀ።

 የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት   ዶክተር ታምሬ ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተማሪዎችን መቀበል የጀመሩት  ቅደመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ነው።

ዩኒቨርሲቲው በአሸባሪው ህወሃት ቡድን  ውድመትና ዘረፋ ቢደርስበትም መልሶ በመጠገንና በማስተካከል ዳግም የመማር ማስተማር ስራውን ለመጀመር ከትናንት ጀምሮ  ተማሪዎችን እየተቀበለ መሆኑን አስታውቀዋል።

አሁን በመጀመሪያው ዙር ከ3 ሺህ የሚበልጡ የአንደኛ፣ የሶስተኛና የአራተኛ ዓመት ተማሪዎችን ለማስተናገድ መቀበል መጀመራቸውን የተናገሩት ዶክተር ታምሬ፤  በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ደግሞ የቀሪ ተማሪዎች ቅበላ ይደረጋል ብለዋል።

የተማሪዎች ማደሪያና መማሪያ ክፍሎች፣ መመገቢያ አዳራሽና ቁሳቁስ፣ ውሃ፣ መብራትና የምግብ ቁሳቁሶች  መሟላታቸውን ገልጸዋል፡፡

''ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተን ባደረግነው ርብርብ ዩኒቨርሲቲው መልሶ ስራ እንዲጀምር አድርገናል'' ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤  ድጋፍ ላደረጉት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ  ተማሪዎች የመቀበል አቅሙን ከ5 ሺህ በላይ   ለማድረስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ዶክተር ታምሬ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም