"ሰራዊቱ ተንከባክቦ ለህክምና አብቅቶናል፤ ከሞትም ታድጎናል"

78

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 3/2014 (ኢዜአ) "ሰራዊቱ ተንከባክቦ ለህክምና አብቅቶናል፤ ከሞትም ታድጎናል" ሲሉ በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት ደርሶባቸው በጦር ኃይሎች ስፔሻላይዝድ አጠቃላይ ሆስፒታል ህክምናቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ዜጎች ይናገራሉ፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን የህዝብ ጠላት መሆኑን በፈጸመው አረመኔ ተግባር አረጋግጧል ብለዋል።

ቡድኑ  በአፋርና በአማራ ክልሎች በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች  የሰው ልጅ ያደርገዋል ተብሎ የማይጠበቅ ግፍ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ፈጽሟል፡፡

የሽብር ቡድኑ ለህጻናት ነፍስ የማይራራ፤ ለእናቶች ልመና እና ተማጽኖ የጥይት ሩምታ ምላሽ የሚሰጥ የግፈኞች ስብስብ መሆኑንም በተግባር አሳይቷል፡፡

የሽብር ቡድኑ አፈ-ቀላጤዎች "ጸባችን ከፖለቲከኞች እንጂ ከህዝብ ጋር አይደለም" የሚል ዲስኩር ሲያስተጋቡ ቢውሉም፤ በተግባር ግን ፀረ-ህዝብ የሆነ ግፍን በመፈጸም ትክክለኛ ግብራቸውን አሳይተዋል፡፡

በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን የሽብር ቡድኑ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች  ደግሞ ለዚህ ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡

በሽብር ቡድኑ ጉዳት ደርሶባቸው ጦር ሃይሎች ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ አጠቃላይ ሆስፒታል ህክምናቸውን እየተከታተሉ ያገኘናቸው የአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪዎች የሽብር ቡድኑን የጭካኔ ጥግ ይናገራሉ፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ አካባቢውን ከተቆጣጠረ በኋላ ለህክምና ወደ ሆስፒታሉ እንዳመጣቸው የሚናገሩት ተጎጂዎቹ፤ "አሸባሪ ቡድኑ ለመናገር ቀርቶ ለማሰብ የሚከብድ ግፍ ፈጽሞብናል" ይላሉ፡፡  

የ27 ዓመት ወጣት ወርቄ ወዳጄ የአምስት እና የአንድ ዓመት ከሶስት ወር እድሜ ያላቸው ህጻናት እናት ስትሆን፤  አሸባሪ ቡድኑ በእሷና በቤተሰቧ ላይ የፈጸመውን ግፍ እንዲህ ትናገራለች፡፡

"ህዳር 29 ቀን 2014 ዓ.ም ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ  የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በር ገንጥለው ገቡ፤ ባለቤቴን እጅና እግሩን በማሰር እኔን ለመድፈር መታገል ጀመሩ" ትላለች፡፡

"እያለቀስኩ ብማጸናቸውም በጀርባዬ ያዘልኩትን ህጻን ልጄን ነጥቀው በመወርወር እኔን መታገል ጀመሩ፤ ይህን ሁሉ ግፍ የሚፈጽሙት እጅና እግሩን ባሰሩት ባለቤቴ ፊት ነው" ስትልም ነው የሽብር ቡድኑን ታጣቂዎች ጭካኔ የገለጸችው፡፡

"ሊይዙኝ ሲታገሉ እምቢ ስላልኳቸው በጥይት ግራ እግሬን መትተው ጣሉኝ" የምትለው ወጣት ወርቄ፤ ባለቤቴ እኔን ሊያተርፍ ከታሰረበት ገመድ ጋር መታገል ሲጀምር በጥይት ሩምታ እኔና ልጆቼ ፊት ገድለውት ሄዱ" ስትልም ነው የተናገረችው፡፡

የስድስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ዘውዲቱ መንገሻም በተመሳሳይ የአሸባሪ ቡድኑ ግፍ ሰለባ ከሆኑት መካከል አንዷ ናቸው፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት፤ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በአካባቢው በወረራ በቆዩባቸው ጊዜያት ሁሉ ወደ ቤታቸው በመምጣት ለልጆቻቸው የጋገሩትን እንጀራ ከህጻናት ጎሮሮ እየነጠቁ ይመገቡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ታዲያ አንድ ቀን  እንጀራ ለመጋገር በሌሊት በተነሱበት አጋጣሚ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በጥይት ሩምታ በመክፈት እጃቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱባቸው ይናገራሉ፡፡

ወጣት ሀዲጋዝ ራህመት ደግሞ "ቤት ውስጥ በተቀመጥንበት መጥተው ካስወጡን በኋላ የሚገድሉትን ገድለው ያቆሰሉትን አቁስለው ጥለውን ሄዱ" በማለት በእርሷና ቤተሰቦቿ ላይ የደረሰውን ግፍ ትናገራለች፡፡

በተተኮሰባቸው ጥይትም በእጇ የየዘችው የአራት ዓመት ህጻን ህይወቱ ሲያልፍ በጀርባዋ ያዘለችው ጨቅላ ህጻን ደግሞ ክፉኛ ተጎድቶ በህክምና ላይ እንደሚገኝ ተናግራለች፡፡

እሷም በግራ ጉንጯ ላይ ክፉኛ የተጎዳች ሲሆን፤ "ወጣትነቴን ቀሙኝ" ስትል በሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች የደረሰባትን ጭካኔ ታስረዳለች፡፡

ተጎጂዎቹ "የመከላከያ ሰራዊቱ ተንከባክቦ ለህክምና አብቅቶናል፤ ከሞትም ታድጎናል" ሲሉም ሰራዊቱ ያደረገላቸውን እንክብካቤ  ይናገራሉ፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ እስኪደርስላቸው ምንም አይነት ህክምና እንዳላገኙም ነው ያስታወሱት።

የመከላከያ ሰራዊት አሸባሪው የህወሃት ቡድንን ከወረራቸው አካባቢዎች ከማስለቀቅ ባሻገር ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ተገቢውን እንክብካቤ በመስጠት ህዝባዊ አለኝታነቱን በተግባር አሳይቷል፡፡

በጦር ሃይሎች ስፔሻላይዝድ አጠቃላይ ሆስፒታል ለከፍተኛ ህክምና የመጡ ሁሉም ተጎጂዎች የሚያረጋግጡትም ይህንኑ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም