ዳያስፖራዎችየክልሉን የተፈጥሮ ሀብት ለማልማት እንደሚፈልጉ አስታወቁ

120

አሶሳ፤ የካቲት 03 / 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ማልማት ላይ በመሳተፍ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚፈልጉ ክልሉን የጎበኙ ዳያስፖራዎች አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባደረጉት ጥሪ መሰረት በርካታዎች ወደ ሀገር ቤት መምጣታቸውንና ይህም  የሀገሪቱን  መልካም ገፅታ ለሌላው ዓለም  ይበልጥ በማስተዋወቅ የውጭን ጫናን  ለመቀነስ  ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል።

በክልሉ ጉብኝት ካደረጉት ዳያስፖራዎች መካከል ከእንግሊዝ ለንደን የመጡት  ወይዘሪት ትዕግስት በቀለ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያን ለመበታተን የተደረገው የሃሰት ዘመቻ ከሽፏል፡፡

ይህም ዳያስፖራው ወደ ሃገር ቤት በመግባት እውነታውን በበለጠ እንድንረዳ አድርጓል፤  በቁጭት ሃገራችንን እንድንደግፍ አነሳስቶናል ብለዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተደረገላቸው አቀባበል እና የተመለከቱት የተፈጥሮ ሃብት አስደሳችና ለማልማትም ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እንዳሉ መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢንቨስትመንትን ከማስፋፋት ጀምሮ የሃገራችንን የቀደመ ስም ለመመለስ በሙሉ አቅማችን ለመረባረብ ዝግጁ ነን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከ15 ዓመታት በላይ በአሜሪካ ቨርጂኒያ እንደኖሩ የሚናገሩት  አቶ ወንድወሰን መላኩ በበኩላቸው፤ በክልሉ ጉብኝታቸው ትንሽ ሃብት በማውጣት ከፍተኛ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል ተረድቻለሁ ብለዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ እና መንግስት ያደረጉላቸው አቀባበል ከዚህ ቀደም ወንድማማች የሆነውን ህዝብ ለመለያየት ሲሰራ የቆየው ሴራ በኢትዮያዊ አንድነት ማክሸፍ መቻሉን አመልክተዋል፡፡

ወደ ሃገራችን የመጣነው በጦርነት የተጎዳውን አካባቢ በመመልከት ለመልሶ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ነው ያሉት ዳያስፖራው፤ ይህንም አቅማቸው በፈቀደ እንደሚተገብሩ ተናግረዋል፡፡

ሃገር በዘላቂነት እንድታድግ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተመለከቱት የኢንቨስትመንት አማራጮች መካከል በግልም ሆነ በቡድን በመደራጀት በሆቴል እና በእርሻ ኢንቨስትመንት የመሳተፍ ፍላጎት አለኝ ነው ያሉት፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ቆታቸው  ደማቅ አቀባበልና መስተንግዶ እንደተደረገላቸው የገለጹት ደግሞ ከካናዳ የመጡት  ዳያስፖራ ወይዘሪት ኤደን ኢሳያስ ናቸው፡፡

በድህነት የቆየነው ሃብት ሳይኖረን ወይም ከየትኛውም የዓለም ማህበረሰብ ስላነስን አይደለም የሚሉት ዳያስፖራዋ፤ አሁን ከፍተኛውን ቁጥር የያዘውን ወጣቱን በማስተባበር የሃገራችንን ሃብት ማልማት የሚገባን ጊዜ ላይ ነን ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ህልውና ለማስጠበቅ ያሳዩትን ትብብር የተፈጥሮ ሃብታችንን ማልማት ላይ መድገም እንሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ይህን ካደረግን በአጭር ጊዜ ከድህንት እንደምንወጣ ተስፋ አለኝ ብለዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ለዳያስፖራዎች ያቀረቡት ጥሪ በትክክለኛ እና በአስፈላጊ ሰዓት ነው ያሉት ወይዘሪት ኤደን ፤ ለጥሪው ፈጣን ምላሽ በመስጠት ወደ ሃገራቸው የመጡበት ምክንያትም ይኸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በአውሮፓ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች የበላይ አስተባባሪ አቶ ሰለሞን አሻግሬ፤ ከፍተኛ የተፈጥሮ ህብት ባለቤት የሆኑ ቤኒንሻጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላን ጨምሮ የሌሎች ክልሎች ህዝብ ከለውጡ በፊት ሃብታቸው ሲዘረፍ መቆየቱን ይናገራሉ፡፡

የክልሎቹ ህዝቦች በአሁኑ ወቅት ከመገፋት ወጥተው በኢትዮጵያዊ አንድነት መቆማቸውን በክልሎቹ ጉብኝታቸው መረዳታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ለውጤቱ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያመሰገኑት አስተያየት ሰጪው፤  ዳያስፖራው አስተምሮ ለዚህ ላበቃው ዜጋው ያለከፈለው ዋጋ አለ ብለዋል፡፡

 ሃብታችንን እና እውቀታችንን በማስተባበር ሃገራንን ከድህነት ለማላቀቅ ለመረባረብ የግድ ነው ሲሉ አቶ ሰለሞን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ እንድሪስ መሃመድ፤ ዳያስፖራው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ምላሽ በመስጠት የተቀመጡ እቅዶችን አሳክቷል ይላሉ፡፡

ዳያስፖራዎች በጦርነት የተጎዱ የአማራ እና አፋር ክልሎችን በመጎብኘት ለመልሶ ግንባታ ያደረጉትን ድጋፍ በመጥቀስ፡፡

ኢትዮጵያ  ሃገራችን ናት፤  ጦርነቱ በዘላቂነት ተጠናቆ ሃገራችን ወደ ቀደመ ሠላሟ ለመመለስ ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝ ኢኮኖሚያችንን ማጠናከር አለብን ብለዋል፡፡

በጦርነት የተጎዱትን በተለይ አማራ እና አፋር ክልሎች በዘላቂነት ማልማት ግዴታችን ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህ ጥረታችን የኢትዮጵያ አንድ አካል የሆነችውን ትግራይንም ያካትታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደር እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ በበኩላቸው፤ ክልሉ በአንዳንድ አካላት የችግር ቀጠና ብቻ ተደርጎ እንደሚታይ ተናግረዋል።

እውነታው ግን ክልሉ የሃገሪቱ እድገት ኮሪደር መሆን የሚያስችለው ህዳሴ ግድብን ጨምሮ የበርካታ ተፈጥሮ ሃብት መገኛ እና ህዝቡም ተከባብሮ የሚኖርበት መሆኑን ለዲያስፖራዎቹ ገልጸውላቸዋል፡፡

ቢሮው ይህን ለማስተዋወቅ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በኢንቨስትመን ዘርፍ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ በሁሉም ኢንቨስትመንት ለሚሳተፉ ዳያስፖራዎች እና ባለሃብቶች በአጭር ጊዜ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም