ዚምባቡዌ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ወዳጅነትና ትብብር ይበልጥ ማጠናከር ትሻለች

84

የካቲት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዚምባቡዌ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ታሪካዊ ግንኙነትና የትብብር ግንኙነት ይበልጥ አጠናክራ መቀጠል እንደምትሻ በኢትዮጵያ የዚምባቡዌ አምባሳደር ታኦንጋ ሙሻያቫኑ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ወቅታዊ ፈተና በራሷ አቅምና ባላት ልምድ እንደምታልፈው ፅኑ እምነት አለን ብለዋል።

ጥር 28 እና 29 ቀን 2014 ዓ.ም በተካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ከተሳተፉ መሪዎች መካከል የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ አንዱ ናቸው።

የመሪዎቹ ጉባኤ ያለምንም ችግር በስኬት የተከናወነ ሲሆን ኢትዮጵያም በክብር የተቀበለቻቸውን እንግዶቿን በክበር ሸኝታለች።

በኢትዮጵያ የዚምባብዌ አምባሳደር ታኦንጋ ሙሻያቫኑ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት የአፍሪካ መሪዎች በአዲስ አበባ ፊት ለፊት ተገናኝተው ስኬታማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ለጉባኤው ስኬታማነት የኢትዮጵያን ብቃት ያደነቁት አምባሳደሩ፤ ዚምባቡዌ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ዚምባቡዌ ከቅኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት ትግል ላይ በነበረችበት ወቅት የነጻነት ታጋይ የሽምቅ ተዋጊዎቿን በማሰልጠን የኢትዮጵያ ውለታ ታሪክ የማይረሳው መሆኑን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ የዚምባቡዌን የተዋጊ ጀት እና አየር መንገድ አብራሪዎች ስልጠና በመስጠትም ሊጠፋ የማይችል አሻራ እንዳላት አምባሳደር ታኦንጋ አንስተዋል።

በመሪዎች ጉባኤ ላይ የታደሙት የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ፤ ኢትዮጵያ መልካም የሚባሉ ለውጦችን እያካሄደች መሆኗን መረዳታቸቸውን አምባሳደሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ዚምባቡዌ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በተለያዩ መስኮች በተለይም በግብርና እና በቱሪዝም መስክ በትብብር እየሰሩ መሆኑን አምባሳደሩ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየቀኑ ወደ ዚምባብዌ በረራ እንዳለው በመግለፅ ይህም የሁለቱን ሀገራት ቱሪዝም ለማጎልበት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የዚምባቡዌ መልካም አጋርና ባለውለታ ናት ያሉት አምባሳደሩ በቀጣይ በትራንስፖርት፣ በማዕድን፣ በአየር መንገድ፣ በሰው ኃብት ስልጠና እና ሌሎችም የሁለትዮሽና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች የሚኖረን ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር መሆኗን ያነሱት አምባሳደር ታኦንጋ፤ አሁን ያጋጠማትን ችግር  ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የመፍታት አቅሙ እንዳላት ዚምባቡዌ ፅኑ እምነት አላት ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን በአገራቸው የማይደራደሩ ጀግኖች ከምንም በላይ ደግሞ ሰላም ወዳድ ህዝቦች መሆናቸውን በቅጡ እናውቃለን ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ማንም የውጭ ሃይል ጣልቃ ሳይገባ ኢትዮጵያ የሚያጋጥማትን ማንኛውንም ችግር የማለፍ አቅሙና ብቃቱ አላት ነው ያሉት።

የዚምባቡዌ ፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ከ35ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

የሁለቱ መሪዎች ውይይት የሀገራቱን ግንኙነት በማጠናከር፣ የትብብር መስኮችን በማስፋት እና በአፍሪካ ሰላምና ፀጥታን በማስፈን ዙሪያ ያተኮረ ነበር።

ኢትዮጵያና ዚምባቡዌ ከሁለትዮሽ ትብብሮች ባሻገር አህጉራዊ ግቦች እንዲሳኩ የበኩላቸውን ሚና የሚወጡ ይሆናል።

የኢትዮጵያና ዚምባቡዌ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከ37 ዓመት በላይ ማስቆጠሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም