የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የታንዛኒያው ዳሬ ሰላም ዩኒቨርሲቲ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

80

የካቲት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የታንዛኒያው ዳሬ ሰላም ዩኒቨርሲቲ በቋንቋ ልማትና ማበልጸግ ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት በትናንትናው ዕለት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃናና የዳሬ ሰላም ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ዊሊያም አናንጊስዬ ተፈራርመዋል፡፡

ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት፤ የአዲስ አበባና ዳሬ ሰላም ዩኒቨርሲቲዎች በአፍሪካ ካሉ ስመ-ጥር የምርምር ተቋማት ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት፣ በጥናትና ምርምር፣ ለአገር እድገት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ በባህል ጥናት ዘርፍ ከሌሎች አገራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

በዚህም ስምምነቱ የምስራቅ አፍሪካ አገሮችን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማሳለጥ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ መጠቀምን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀጠናው ሰፊ ተናጋሪ ህዝብ ያለውን የኪስዋህሊኛ ቋንቋ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ለማስተማር ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኪስዋህሊኛ ቋንቋ ትምህርት መስጠቱ የኢትዮጵያን ህዝብ ከምስራቅ አፍሪካ ህዝብ ጋር በቀላሉ ለማቀራረብ ያግዛል ብለዋል፡፡

ስምምነቱ ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች በኪስዋህሊኛ ቋንቋ ላይ በጋራ ጥናትና ምርምር እንዲያካሂዱ በማገዝ ለሁለቱ አገሮች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር መጎልበት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የዳሬ ሰላም ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ቦናቬንቸር ሩቲንዋ በበኩላቸው ስምምነቱ በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል መቀራረብና ወንድማማችነትን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል፡፡

የኪስዋህሊኛን ቋንቋ የምስራቅ አፍሪካ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ከማድረግ ባለፈ ተጨማሪ ጥናትና ምርምር ለማካሄድ እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡

የዳሬ ሰላም ዩኒቨርሲቲ ከጋና፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኡጋንዳና ግብጽ የመጡ ተማሪዎችን ሙሉ ወጪ በመሸፈን በመጀመሪያ፣ ሁለተኛና በሶስትኛ ዲግሪ እያስተማረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በዳሬ ሰላም ዩኒቨርሲቲ የኪስዋህሊኛ ቋንቋ ለመማር ለሚመጡ ኢትዮጵያውያን ነጻ የትምህርት እድል ማመቻቸቱንም ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ባመቻቸው ነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ጥቅማቸውን አስከብረን እንዲማሩ እናደርጋለን፤ የስምምነቱ ዓላማም ይሄው ነው ብለዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም