የውጭ ጫናን በመቋቋም የሀገራችንን ልማት ለማረጋገጥ በፍቅርና በትብብር መስራት ይገባል- ዳያስፖራዎች

79

ዲላ፤ የካቲት 1/2014 (ኢዜአ) የውጭ ጫና በዘላቂነት በመቋቋም የሀገርን ልማት ለማረጋገጥ በፍቅርና በትብብር መስራት እንደሚገባ በጌዴኦ የዘመን መለወጫ "ዳራሮ " በዓል ላይ የተሳተፉ ዳያስፖራዎች ተናገሩ።

ከበዓል ተሳታፊዎች  መካከል ከካናዳ ቫንኮቨር ከተማ የመጡት አቶ ካሌብ ግርማ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤  የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ውስጥ  መግባታቸውን አውስተው፤  በዳራሮ በዓል  ላይ ሲታደሙ የመጀመሪያቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

በበዓሉ ከቦረና፣ ከጉጂ፣ ከሃላባ፣ ኮንሶና ከሌሎችም አካባቢዎች የመጡ ወንድም ህዝቦች በዓሉን በጋራ ሲያከብሩ በማየታቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ነው ያመለከቱት።

''ይህም እርስ በእርስ  ያለንን ግንኙነትና ህብር ከማጠናከር ባለፈ ህዝቦችን በመለያየት ሀገራችንን ለማፍረስ የሚሰሩ ሃይሎችን ሴራ ለማክሸፍ እና ለማሳፈር ገንቢ ሚና አለው'' ብለዋል።

ይህንን እሴት አጋዥ በማድረግ ማንኛውንም የውጭ ጫና  በዘላቂነት በመቋቋም የሀገርን ልማት ለማረጋገጥ  በፍቅርና በትብብር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የብዙ ባህሎች ባለቤት መሆኗን የጠቀሱት አቶ ካሌብ፤ በተለይ ባህላዊና መንፈሳዊ የአደባባይ በዓላትን ከማስተዋወቅና ሀብት ከማመንጨት አንጻር  መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የአንዳንድ ምዕራባዊያንን ጫና በዘላቂነት ለመቋቋም ልዩነቶችን በማጥበብ ሀገራዊ አንድነታችንን በማጉላት የሀገርን እድገት ለማረጋገጥ በርትተን መስራት አለብን ያሉት ደግሞ ከሳዑዲ አረቢያ የመጡት አቶ መዋባ ሸኩር ናቸው።

ከ15 ዓመታት የውጭ ሀገር ቆይታ በኋላ  ዳራሮ በዓልን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በተገኙበት በድምቀት  ሲከበር በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

''የቋንቋና የሐይማኖት ልዩነታችን የመከፋፈልና የግጭት ምንጭ እንዲሆን የተሰራብንን ሴራ አክሽፈን ዛሬ የአንዱ በዓል የእኛ ነው በሚል ዳራሮን ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን በሚያሳይ መልኩ መከበሩ ልዩ ስሜት ፈጥሮብኛል'' ብለዋል።

ከቻይና የመጡት ወይዘሮ ቅድስት ፍንታሁን፤ ባህላዊና ሐይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት በፍቅርና በመተሳሰብ በጋራ መከበራቸው የውጭ ሚዲያዎችን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ያጋለጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሀገር ውስጥ የአደባባይ በዓላት ባለፈ አህጉራዊ መድረክ የሆነውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ማስተናገዷ ጫናዎችን መቋቋም የምትችል ሀገር መሆኗን የሚያሳይ እንደሆነም አመልክተዋል።

የአንዳንድ ምዕራባዊያንን ጫና በዘላቂነት ለመቋቋም ፍቅራችንን በማጠናከር በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

ዳራሮን በጋራ ማክበራችን አንድነታችንን ከማጠናከር ባለፈ አንዱ የሌላውን ባህልና ወግ እንዲያውቅ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ነው ያሉት ወይዘሮ ቅድስት፤ ወጣቱ ትውልድም ባህሉን በመንከባከብ ጠብቆ ማቆየት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የዘንድሮው የጌዴኦ  ዘመን መለወጫ የ"ዳራሮ"  በዓል የተለያዩ ብሔር ብሔረሰብ ተወካዮችና የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ሰሞኑን በዲላ ከተማ  በድምቀት መከበሩን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም