በማኦኮሞ ልዩ ወረዳ በአሸባሪው ሸኔ ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን ነጻ ማድረግ ተቻለ

76

አሶሳ፣ የካቲት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማኦኮሞ ልዩ ወረዳ በተካሄደ የተቀናጀ የሠላምና ፀጥታ ስራ በአሸባሪው ሸኔ ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን ነጻ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አሸባሪው ሸኔ ከሁለት ወራት በላይ በልዩ ወረዳው ተደጋጋሚ ጥቃት በመፈጸም በንጹሃን ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

የሽብር ቡድኑን ጥቃት በመሸሽ በርካታ ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉ የገለጹት አቶ ሙሳ፤ የልዩ ወረዳውን አስተዳደር ጽህፈት ቤትን ጨምሮ የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት በአሸባሪው ቡድን መውደማቸውን ገልጸዋል።

ቡድኑ ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ የሚመላለሱ የህዝብ እና የመንግስት ተሽከርካሪዎችን በማስቆም ንጹሃንን አግቶ በመውሰድ እንዲሁም ወደ ክልሉ የሚገቡ ነዳጅ፣ ሸቀጣሸቀጥ እና የምግብ እህል ሲዘርፍ እንደነበር ተናግረዋል።

እንዲሁም በልዩ ወረዳው ቶንጎ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው ጎሬ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በቡድኑ ተዘርፎ ስደተኞች ከአካባቢው መውጣታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የሀገር መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ኃይልና የአባባቢ ሚሊሻ በቅንጅት ባደረጉት ዘመቻ አካባቢውን ከሽብር ቡድኑ ማጽዳት ተችሏል ብለዋል። 

በተካሄደው የተቀናጀ የሠላምና ፀጥታ ስራ 27 የሽብር ቡድኑ አባላት ሲደመሰሱ፤ 35 ቆስለው መያዛቸውን ገልጸው፤ ሌሎች 13 ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የጦር መሳሪዎች መማረካቸውን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት ልዩ ወረዳው በተቀናጀ የፀጥታ አስከባሪ ኃይል  ቁጥጥር ስር በመዋል የአካባቢው ሠላም መመለስ መቻሉን  አስታውቀዋል።

በሽብር ቡድኑ የደረሰውን ጠቅላላ ጉዳት በመለየት መልሶ ለማቋቋም የክልሉ መንግሥት እንቅስቀሴ መጀመሩን ገልጸው፤ የልዩ ወረዳው አስተዳደራዊ መዋቅር መልሶ ተደራጅቶ ስራ እስኪጀምር ድረስ ልዩ ወረዳው በተቀናጀ የፀጥታ አስከባሪ ኃይሉ እንዲመራ የክልሉ መንግሥት መወሰኑን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም