የሙስና ተግባር ሲፈፀም የሚያጋልጥ፣ የሚታገልና ለሕዝብ ጥቅም የሚቆም ማሕበረሰብ የሚፈጥር ዘገባ መሰራት ይኖርበታል

80

የካቲት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) በየትኛውም መስክ የሙስና ተግባር ሲፈፀም የሚያጋልጥ፣ የሚታገልና ለሕዝብ ጥቅም የሚቆም ማሕበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችሉ ዘገባዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተጠቆመ።

ሙስናንና ብልሹ አሰራርን በጋራ መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ባለቤቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ዶክተር ሙላቱ አለማየሁ ባቀረቡት ጽሑፍ፤ መገናኛ ብዙሃን ሙስናን የሚፀየፍና የሚታገል ትውልድ በመቅረጽ ረገድ ሰፊ ስራ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃኑ ባለሙያዎች የሚሰሯቸው የምርመራና ሌሎች ዘገባዎች ሕብረተሰቡን የሚያነቁ፣ የሚያስተምሩና ሙስናን እንዲታገሉ የሚያስችሉ መሆን አለባቸው ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን ጥልቅ ምርመራዎችን በመስራት፣ የተፈፀሙ ሙስናዎችን በማጋለጥ፣ ለህብረተሰቡ በማሳየትና ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡ በመታገል በኩል ትልቅ ሚና እንዳላቸው አስገንዝበዋል።

''ሙስና እየተከሰተ ያለው በገንዘብ ብቻ አይደለም ሙስና በአዕምሯአችንም ገብቷል፣ በሰዓት አጠቃቀም፣ የሰብዓዊ መብትና ሌሎችንም ችግር እያስከተለ ይገኛል'' ነው ያሉት ዶክተር ሙላቱ። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፍትህ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጽዋዬ ሙሉነህ በበኩላቸው፤ ሙስናን የማጋለጥ፣ የመታገልና የመከላከል ስራ ውጤታማ የሚሆነው ሁሉም ዜጋ በየተሰማራበት በጋራ ሲንቀሳቀስ ነው ይላሉ።

የሙስና አፈፃፀም ስልት በየወቅቱ መልኩንና ቅርጹን የሚቀይር በመሆኑ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በማስከተል ላይ ይገኛል ብለዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች ጋዜጠኞቻቸው የምርመራ ስራዎች ላይ እንዲያተኩሩና የፀረ-ሙስና ትግሉን እንዲያግዙ ማዘበረታታት አለባቸው የሚለው ደግሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ነው።

ባለሙያዎቹ ለሕዝብ የሚያስተላልፏቸው መረጃዎች ሙስናን የሚታገሉና የሚያጋልጡ እንዲሆኑ ለማድረግ ከተለያዩ ጫናዎች እንዲወጡና ከለላ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል።

የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ የቦርድ ሊቀመንበር ዶክተር ኢንጅነር ብርሃኑ አሰፋ በበኩላቸው በሀገሪቱ በየደረጃው በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ግልጽነትን በማስፈን ሙስናን መዋጋት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈስን ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን ሚና የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም