በመዲናዋ ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ከባድ ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች በህብረተሰቡ ትብብር እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል

85

አዲስ አበባ የካቲት 01/2014(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ከባድ ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች በህብረተሰቡ ትብብር እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባለፉት ስድስት ወራት ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ሥራ በመሥራቱ ለሕዝቡ ሥጋት የነበሩ ከባድ ወንጀሎች እየቀነሱ መምጣታቸውን ገልጿል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት በመዲናዋ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ተግባር በስፋት እየተከናወነ በመሆኑ ለውጥ እየታየ ይገኛል።

በተለይም ባለፉት ስድስት ወራት ለከተማዋ ሥጋት የነበሩ ከባድ ወንጀሎችን ለመቀነስ በተደረጉ ሥራዎች ኅብረተሰቡ ዋነኛ የፖሊስ ተባባሪ እንደነበር አስታውሰዋል።   

በዚህም በስድስት ወራት ብቻ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት በህብረተሰቡ ጥረት እጅ ከፍንጅ መያዙን ኮማንደር ፋሲካ ገልጸዋል፡፡

በህልውና ዘመቻው ኅብረተሰቡ አካባቢውን በመጠበቅ የተለያዩ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ሲከላከል መቆየቱንም ገልጸዋል።

የጦር መሳሪያዎች፣ ሐሰተኛ የብር ኖቶችና የመገናኛ ሬዲዮኖች ጭምር በኅብረተሰቡ ጥቆማና ትብብር መያዛቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም ኅብረሰተቡን የፀጥታው ባለቤት እንዲሆን ፖሊስ እቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ያለው ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ እንዲሆን የህዝቡ ትብብርና ተሳትፎ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም