አፍሪካን የሚወክል ጠንካራ ሚዲያ ማቋቋም ጊዜ ሊሰጠው አይገባም

78

አዲስ አበባ የካቲት 1/ 2014 (ኢዜአ) አፍሪካን የሚወክል ጠንካራ ሚዲያ የማቋቋም ጉዳይ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ የግሎባል ቴሌቪዥን ኔትወርክ አፍሪካ መስራችና የሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘጋቢ ጋዜጠኛ ግሩም ጫላ ገለጸ።
በ35ተኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ "የአፍሪካ ድምጽ የሚሰማባት፣የፓን አፍሪካዊነት ድምጽ የሚንጸባረቅባት የጋራ አህጉራዊ ሚዲያ ሊኖረን ይገባል" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ይህም አንዳንድ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ሆነ ብለው የአፍሪካን ገጽታ ለማበላሸት የሚያደርጉትን ዘመቻ ለመከላከል ያስችላል ነው ያሉት፡፡

"የግሎባል ቴሌቪዥን ኔትወርክ ኦፍ አፍሪካ" መስራችና የቻይና ዓለም አቀፍ ቴሌቭዥን ኔትወርክ (ሲጂቲኤን) ዘጋቢ ግሩም ጫላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት ሃሳብ ወቅታዊና ትክክለኛ መሆኑን ለኢዜአ ተናግሯል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ መገናኛ ብዙሃን የጦርነት ሜዳ እየሆኑ በመምጣታቸው ጉዳዩ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፤ አፍሪካም የራሷን ተጽእኖ ፈጣሪ ሚዲያ በማቋቋም ጥቅሟን ማስከበር አለባት ብሏል፡፡

አፍሪካ በራሷ ድምጽ መናገር አለባት ያለው ጋዜጠኛ ግሩም ጫላ፤ የአፍሪካን አቅም ብቻ በመጠቀም ይህንን ውጥን እውን ማድረግ እንደሚቻል አብራርቷል፡፡

በመሆኑም አህጉሪቷን የሚወክል ጠንካራ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም በማቋቋም የአፍሪካን ትንሳኤ ማረጋገጥ ይገባል ነው ያለው፡፡

በተለይ ለአፍሪካውያን የነፃነትና የሉዓላዊነት ምልክት የሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በራሳቸው አቅም አለም አቀፍ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት መኖር እንዳለበት ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም