የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና አፍሪ-ኤግዚም ባንክ የ1 ቢሊየን ዶላር ብድር ማግኘት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

152

አዲስ አበባ የካቲት 1/ 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና አፍሪ-ኤግዚም ባንክ የ1 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ብድር ማግኘት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ እና የአፍሪ-ኤግዚም ባንክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ቤኔዲክት ኦርማህ ፈርመዋል።

የተደረገው ስምምነትም የንግድና ኢንቨስትመንት፣ በስራ እድል ፈጠራና በድህነት ቅነሳ ለሚደረጉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

ኢትዮጵያን ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር የኢንቨስትመንት ትስስሯን እንድታጠናክር ለማስቻል እገዛ ይኖረዋልም ነው የተባለው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፤ ከባንኩ ጋር የተደረገው ስምምነት በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ የንግድና ኢንቨስትምንት ስራዎች ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገለጸዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ ተግባራዊ ሲደረግም ባንኩ ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ የብድር ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የአፍሪ-ኤግዚም ባንክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ቤኔዲክት ኦርማህ፤ ባንኩ የአፍሪካን አጀንዳ በ2063 ለማሳካት ያስቀመጠቸውን የልማት ግቦች ከዳር ለማድረስ ይሰራል ብለዋል።

የኢንፖርት ኤክስፖርት ባንክ የሆነው አፍሪ-ኤግዚም ባንክ እ.ኤ.አ. በ1993 በአፍሪካ ልማት ባንክ ስር የተፈጠረ የፓን አፍሪካ ባለብዙ ወገን የንግድ ፋይናንስ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም