የህዝብን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሚመልስ አመራር መገንባት ወሳኝ ነው- የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ

197

ሀዋሳ ጥር 30/ 2014 (ኢዜአ) የህዝብን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በአግባቡ ተረድቶ የመመለስ ብቃት ያለው የአመራር ስርዓት መገንባት ወሳኝ መሆኑን የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ ተናገሩ ።

ለሶስት ቀናት የሚቆየው የሀዋሳ ከተማ መካከለኛ አመራሮች የግምገማ  መድረክ ተጀምሯል።

" መመረጥ ተለውጦ ሀገርን ለመለወጥ” መሪ ሀሳብ በተጀመረው መድረክ ላይ የተገኙት ዋና አፈ ጉባኤዋ፤  ባለፉት 27 ዓመታት በህዝብ ላይ የተጫነውን ቀንበር ለማስወገድ የተደረገው ህዝባዊ ትግል ፍሬ አፍርቶ የለውጥ ምዕራፍ መጀመሩን አስታውሰዋል።

ለውጡ ህዝቡ በሚፈልገው መልኩ በመምራት ያደሩ ጥያቄዎች በመመለስ የሀገሪቱን ዘላቂ የብልጽግና ግቦች ማሳካት የሚጠበቅ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም የማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በአግባቡ ተረድቶ መመለስ ያልቻለ አመራር መኖሩን ጠቁመዋል።

እግራቸውን በሁለት ቦታ እየረገጡ የለውጡ ሂደት ለማደናቀፍ የሚሞክሩ እንዳሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት ጉዞ ለመለየት ጥረት መደረጉን አመልክተው፤ እነዚህን በማጣራት ተገቢ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

ልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በፍትሃዊነት ተደራሽ ማድረግ የሚችል አመራር በመገንባት ሀገሪቱ ያቀደችው ዘላቂ የብልጽግና ጉዞ ማሳካት የመንግስትና ህዝቡ በምርጫ ዕድል የሰጠው መሆኑንም ጠቁመዋል።

 የብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በበኩላቸው፤ ህዝቡ የሚፈልገው አገልግሎት በመስጠት  እርካታውን  ማረጋገጥ የሚችል አመራር ለመገንባት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ባለፉት በሶስት የለውጥ ዓመታት ያሳካቻቸው ትላልቅ ግቦች እንዳሉ ሁሉ በተጀመረው ልክ ልማቱና ለህዝብ ጥያቄ ምላሾች እንዳያገኙ ሲያደናቅፉ የነበሩ አካላት መስተዋላቸውን  አንስተዋል ።

በተለይም በሙስናና ብልሹ አሰራሮች የተተበተቡ ከህዝብ የተሰጣቸውን የመሪነት ሚናን ወደጎን በመተው የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት አቋራጭ መንገድ የመረጡ በግምገማ ተጣርቶ የመተካትና ተጠያቂ የማድረግ ስራ ይሰራል ብለዋል ።

ባለፈው ዓመት በተደረገው ምርጫ ከነጉድለቱ የብልጽግና ፓርቲን ህዝቡ የመረጠው የተጀመሩ የልማትና ሌሎች ትልልቅ ግቦች አሳክቶ ሀገሪቱን የቀደመ ገናናነት ይመልሳል በሚል መሆኑን አውስተዋል።

ይህን ለማሳካት ደግሞ አመራሩ ራሱ በለውጡ የተቃኘና ሌላውን የሚለውጥ እንዲሆን ማድረግ ይደር የማይባል ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

እስከታች ድረስ ያለው አመራርና አባላት በየአከባቢው የሚነሱ የህዝብ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችና ሌሎች አገልግሎቶች ቅሬታዎች ለቅሞ መመለስና እርካታን ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ራሱን ለመለወጥ ዝግጁ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

አመራሩ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ማቀጣጠልና የህዝብ የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ቁመና ለመገንባት መድረኩ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር  ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ካሱ አሩሳ ናቸው።

በተለይም በህዝብ ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎች በተደራጀና በተቀናጀ የሚመልስ፣ ያለውን ውስን ሀብት በአግባቡ የሚጠቅምና ለህዝብ ተጠቃሚነት የሚሰራ ለመሆን አመራሩ መዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል።

የግምገማው መድረክ  ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤  ተመሳሳይ መድረኮች በክልሉ ሌሎች የተለያዩ መዋቅሮች መቀጠላቸውም ተመልክቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም