ሚኒስቴሩ የሴቶችን የስራ እድል ተጠቃሚነት ለማሻሻል በትኩረት መስራት አለበት

128

ጥር 30/2014 (ኢዜአ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሴቶችን የስራ እድል ተጠቃሚነት ለማሻሻል በትኩረት መስራት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ፡፡
በምክር ቤቱ የሰው ሀብት ልማት ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን የስድስት ወራት አፈፃጸምን ገምግሟል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ በኢትዮጵያ ካለው የስራ ፈላጊ ዜጎች ቁጥር አንጻር የስራ እድል ፈጠራ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል፡፡

የስራ እድል ፈጠራ ተግባራት ሴቶችንና በገጠር የሚኖሩ የኀብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንዲያደርግም ነው የተናገሩት፡፡

ሚኒስቴሩ የስራ ፈላጊ ዜጎችን የሚያሳይ መረጃ በማደራጀትና ለስራ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ዜጎችን የስራ ውል በማጽደቅ ወደ ስራ እንዲሰማሩ ያደረገው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

ይሁንና ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የመስሪያ ቦታ በማመቻቸት ረገድ ክፍተት መኖሩን ገልጸው፤ ሚኒስቴሩ በጉዳዩ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራም ነው ያሳሰቡት፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የመስሪያ ቦታ ማመቻቸት የበርካታ ተቋማትን ቅንጅት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት በተገቢው መልኩ ሚኒስቴሩን እየደገፉት አለመሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

በተጨማሪ በአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ማህበራት ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ በመሸጋገር  የተሰጣቸውን የመሥሪያ ቦታ ለተተኪዎች ያለመልቀቅ ፍላጎት ማሳየታቸውንና ይህም በዘርፉ ላይ እክል መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በቋሚ ኮሚቴው የተነሱ ሃሳቦችን እንደግብዓት በመውሰድ በቀጣይ ለማስተካከል እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም