ህዝቡ በድርቅ የተጎዱ ወገኖቹን ለመታደግ እያከናወነ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ ነው - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

118

ሐረር፤ ጥር 30/ 2014 (ኢዜአ) በሶማሌ ክልል ህዝቡ በድርቅ የተጎዱ ወገኖቹን ለመታደግ እያከናወነ ያለው የድጋፍ ስራ የሚበረታታ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቷ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሃመድ በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ አካባቢያቸውን ለቀው የመጡ ነዋሪዎችን እና እንስሳትን ተመልክተዋል፤ በቀብሪበያህ ከተማ በድርቁ ተፈናቅለው ከመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋርም ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት ፕሬዚዳንት  ሳህለወርቅ ዘውዴ  እንደተናገሩት፤  የክልሉ ህዝብ በድርቅ የተጎዱ ወገኖቹን ለመታደግ እያከናወነ የሚገኘው ተግባር የሚበረታታ እና ምስጋና የሚገባው ነው።

በተለይ ህዝቡ  የመደጋገፍ ስራን ማከናወኑ የዜጎችን ህይወት መታደግ ማስቻሉን ጠቅሰው፤ ይህ የክልሉ መልካም እሴት የሆነው የመደጋገፍ ባህል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ተጎጂዎችን መመልከት እና ማነጋገሩ የጉዳቱ ሁኔታ መንግስት በጥልቀት ተረድቶ በቀጣይ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

እንዲሁም አለምአቀፍ ለጋሽ ሀገራት ፍትሃዊና ሚዛናዊ የሆነ ሰብአዊ እርዳታ አሰጣጥን እንዲተገብሩም እንዲሁ።

የክልሉ መንግስትም በሰላምና ልማት ላይ እያከናወነ የሚገኘውን አበረታች ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሃመድ በበኩላቸው፤ በሶማሌ ክልል የተከሰተውን ድርቅ ባህሪ እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሁናዊ ሁኔታ እየተከታተለ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ላይ መንግስት በትኩረት መስራቱ ተገቢና አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም አስፈላጊው የሰብዓዊ እርዳታ የሚደረግበትን ሁኔታ ከመንግስት ጋር እንደሚወያይ እና በጋራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የሱማሌ  ክልል ርዕሰ መስተደድር  ሙስጠፌ ሙሀመድ በበኩላቸው፤ የቀብሪበያህ ህዝብ ለተጎጂ ወገኖች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው፤ የክልሉ መንግሥትም የተለያዩ አካላትን በማስተባበር የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት የህብረተሰብ ተወካዮዎች በአሁኑ ወቅት የውሃ፣የእንስሳት መኖና የምግብ እጥረት እንዳለባቸው ጠቅሰው ፤ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የልዑካን ቡድኑ በጅግጅጋ ከተማ የተከናወኑ የመንገድ እና ሌሎች  የልማት ስራዎችን ጎብኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም