አመራሩ ለብልጽግና ጉዞ ስኬት እራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል

60

ዲላ፤ ጥር 30/2014 (ኢዜአ) አመራሩ የተግባርና የአመለካከት አንድነት በመፍጠር ለቀጣይ ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ስኬት እራሱን ሊያዘጋጅ እንደሚገባ ተመለከተ።
"መመረጥ ተለውጦ ሀገርን ለመለወጥ " መሪ ሀሳብ  ለጌዴኦ ዞን አመራሮች የተዘጋጀ የግምገማ መድረክ በዲላ ከተማ ተጀምሯል።

በመድረኩ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራር ዶክተር አበባየሁ ታደሰ ፤ህዝቡ ለብልጽግና ፓርቲ በምርጫ የሰጠው ድምጽ ድልም እድልም ነው ብለዋል

ይህን ህዝብ የሰጠውን እድል በአግባቡ በመጠቀም ቀጣዩ ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በሚያስችል አቅምና አቋም ራሳችንን ልናዘጋጅ ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።

በተለይ  የመልካም አስተዳደር ችግሮች ፈጥኖ በመፍታት የህዝቡን የመልማት ፍላጎት ለማሟላትና ሀገራዊ ለውጡን ለማፋጠን መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል

በመድረኩም ጥልቅ ግምገማ በማድረግ ወጣ ገባ የሚለውን የአመራር ቁመና ከማስተካከል ባለፈ የተግባርና የአመለካከት አንድነት መፍጠር እንዳለበትም ተናግረዋል።

በተለይ ብልጽግና እራሱን ስለማደሱ አንዱ መገለጫ የሆነውን ነጻና ዴሞክራሲያዊ ውይይት በማድረግ ገዥ ሃሳብ የሚወጣበትና የአመራር አቅም የሚገነባበት እንዲሆን ሁሉም በንቃት መሳተፍ እንደሚጠበቅበትም  አሳስበዋል።

መድረኩ ለቀጣይ አራት ቀናት በሚያደርገው ቆይታ  መመረጥ ተለውጦ ሀገርን ለመለወጥ የሚለውን ጨምሮ የተለያዩ ሰነዶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው የገለጹት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ የጌዴኦ ዞን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተወልደ ተስፋዬ ናቸው።

አመራሩም መድረኩን በመጠቀም የቀጣይ ሀገራዊ ተልዕኮ መወጣት በሚያስችል መልኩ አቅሙን ለመገንባት መዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም