የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ከነዋሪዎችና ከሌሎች አካላት ጋር ባደረገው የተቀናጀ ስራ የመሪዎች ጉባኤ ያለምንም ችግር ተጠናቋል

166

አዲስ አበባ ጥር 30/2014 የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ከከተማው ነዋሪና ከሌሎች አካላት ጋር ባደረገው የተቀናጀ ስራ የመሪዎች ጉባኤ ያለምንም ችግር መጠናቀቁን የጸጥታና ደንነት የጋራ ግብረ -ኃይል አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረውን 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በማስመልከት የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ -ኃይል የማጠቃለያ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ- ኃይሉ ከከተማው ነዋሪና ከሌሎች አካላት ጋር ባደረገው የተቀናጀ ስራ ጉባኤው ያለምንም የጸጥታ ችግር በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።   

ጉባኤው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ያለምንም እንከን እንዲካሄድ በዲሲፕሊን የተመራ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አስታውሰዋል።

ከመከላከያ፣ የሪፐብሊካን ጥበቃ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የአዲስ አበባ ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስን ያካተተ ብሔራዊ የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በማቋቋሞ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰዋል።

የአሸባሪዎቹ ሸኔና ህወሓት ኢትዮጵያን የማተራመስ እቅድ የማይሳካ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ጀነራሉ የእነርሱ ርዝራዦች አጋጣሚውን ተጠቅመው ከተማዋን እንዳያውኩ በቅንጅት መሰራቱን ተናግረዋል።   

ለጉባኤው ስኬት የከተማው ነዋሪ፣ ሌሎች የተለያዩ አካላት ከጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ሃይል ጋር በመተባበር ላደረጉት የላቀ አስተዋፅኦ ኮሚሽነር ጀነራሉ አመስግነዋል።

የጋራ ግብረ-ኃይሉ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ አገልግሎት ላይ ያልዋሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጉባኤው በሰላም እንዲካሄድ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።

በተለይ በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያና በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ ጊዜያዊ ቢሮ ከፍቶ የጸጥታና ደህንነት ስራዎችን ማከናወኑ የጸጥታው ስራ የበለጠ እንዲሳለጥ አድርጓል ብለዋል።

ለጉባኤው ሰላማዊነት ከ40 ሺህ በላይ የጸጥታ አካላት በአዲስ አበባ መሰማራታቸውንም ነው ያስታወሱት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ፡፡

ግብረ ሃይሉ፤ የከተማው ነዋሪ፣ የአገሪቱ የጸጥታ ሃይል፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአፍሪካ ህብረት አመራርና ሰራተኞችና  ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንግዶቹ ወደ አገር ቤት ገብተው እስኪመለሱ ላሳዩት ትዕግስትና ትብብር ምስጋና አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም