ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ሁሉን አቀፍ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ 411 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል

75

ጥር 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ አህጉር ነፃ የንግድ ቀጠና የአህጉሪቱን የትራንስፖርት መሰረተ ልማት በመጨመር የንግድ ትስስሩን በእጥፍ ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሀፊ ዶክተር ቬራ ሶንግዌ ገለጹ።

ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ሁሉን አቀፍ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ 411 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋልም ብለዋል።

አምስተኛው የአፍሪካ አህጉር ቢዝነስ ፎረም "የአፍሪካ አህጉርን ነፃ የንግድ ቀጠና ለማሳለጥ የአየር ትራንስፖርትና ቱሪዝምን መሰረት ያደረገ ሁሉን አቀፍ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት እንገንባ" በሚል መሪ ሃሳብ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ተካሂዷል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ዶክተር ቬራ ሶንግዌ እንዳሉት፤ የአፍሪካ ዝቅተኛ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት እርስ በርስ የንግድ ምጣኔ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።

በአህጉሪቱ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ተገንብቶ ነፃ የንግድ ቀጠናው እውን ሲሆን የአፍሪካ የእርስ በእርስ ንግድ ትስስር 40 በመቶ ያድጋል ብለዋል።

በአፍሪካ ምድር ሁሉን አቀፍ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ለመገንባት ነፃ የንግድ ቀጠናውን እውን ለማድረግ እስከ 411 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያስፈልጋል ብለዋል።

የነፃ የንግድ ቀጠናው ለአህጉሪቱ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው የገለጹት ዶክተር ቬራ፤ ጥቅሙን ማግኘት የሚቻለው ግን አህጉራዊው የመሰረተ ልማት እውን ማድረግ ሲቻል ነው ብለዋል።

በትራንስፖርት መሰረተ ልማት ዘርፍ ለጭነት ተሽከርካሪዎች ግዢ 345 ቢሊዮን ዶላር፣ ለአውሮፕላን ገዥ 25 ቢሊዮን፣ ለባቡር ፉርጎዎች ገዥ 36 በሊዮን፣ ለመርከብ ገዥ 4 ቢሊዮን፤ በድምሩ እስከ 411 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል ብለዋል።

"ስለ ሁሉን አቀፍ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ስናወራ በነፃ የንግድ ቀጠናው ስለምንፈጥረው 600 ሚሊዮን የስራ እድል፣ በአንዳንድ እንደ ጋምቢያ ያሉ ሀገሮች እስከ 15 በመቶ የሀገራቸውን ጂዲፒ የያዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ስለማሳደግ ነው" ብለዋል።

ምዕራብ አፍሪካዊት ሀገር ጋምቢያ የአየር መንገድ የሌላት ብትሆንም በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠር ጎብኝ ታስተናግዳለች፤ የሁሉን አቀፍ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ስንል ይሄንን የቱሪዝም ዘርፍ ማነቃቃት እንደሆነ ይታወቅልን ብለዋል።

በአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር ዶክተር አማኒ አቡ-ዘይድ፤ የአፍሪካ የትራንስፖርት አገልግሎት ከዓለም አገራት ጋር ሲነፃፀር በጣም ውድ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአፍሪካውያን የአቬዬሽን ኢንዱስትሪ ለአደጋ ጊዜና ለሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት በጣም ያስፈልጋል፤ በተለይ የባህር በር ለሌላቸው አገሮች ይበልጥ ተመራጭ ነው ብለዋል።

የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ባቡር፣ የብስ አፍሪካን በንግድና ምጣኔ ሃብት እርስ በእርስ ለማስተሳሰር ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ወጭን ከመቆጠብም ባለፈ የንግድ ልውውጡን በማሳለጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ያደርጋል ተብሏል።

የአፍሪካ አህጉር ነፃ የንግድ ቀጠና የአፍሪካ አገራትን የኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ በማሳደግ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ እንደሚያግዝም ተገልጿል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም