በሰሜን ኢትዮጵያ ለአውሮፕላን በረራ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ፈጥሮ የነበረው የአቧራ ብናኝ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ይጠፋል

51

አዲስ አበባ ጥር 30/2014 በሰሜን ኢትዮጵያ ለአውሮፕላን በረራ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ፈጥሮ የነበረው የአቧራ ብናኝ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት እንደሚጠፋ የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።
በኤጀንሲው የትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ጫሊ ደበሌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ጥቃቅን የአቧራ እንክብሎች በአየር ላይ በመንሳፈፋ በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ፈጥረው ቆይተዋል፡፡

ይህም ወደ ባህርዳርና ጎንደር የሚደረገውን የአውሮፕላን በረራ አስተጓጉሎ የቆየ ሲሆን፤ በረራው በዛሬው እለት ዳግም ተጀምሯል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገላጻ፤ የአቧራ ብናኙ የተከሰተው መነሻውን ሱዳን ባደረገ ጠንካራ ነፋስ ነው፡፡

በዚህም ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜናዊና ምዕራባዊ አካባቢዎች እንዲሁም በትግራይ ምስራቃዊ ክፍል አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ መከሰቱን ነው የተናገሩት፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ለአውሮፕላን በረራ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ፈጥሮ የነበረው የአቧራ ብናኝ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት እንደሚጠፋም ነው ያስረዱት፡፡

የአቧራ ብናኙ በጤና ላይ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል ኀብረተሰቡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል(ማስክ) እንዲጠቀምም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም