ወደ አገር ቤት ከመጡ የዳያስፖራ አባላት 22 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ተችሏል

67

አዲስ አበባ ጥር 30/2014 አገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ የዳያስፖራ አባላት በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ 22 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።
እስካሁን ባለው ሂደት 490 ዳያስፖራዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ስራ መጀመራቸውንም ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተቀብለው በርካታ ዳያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በተለያዩ ሁነቶች ሲሳተፉ እንደነበር ይታወቃል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሃመድ እንድሪስ አገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ወደ አገር ቤት የመጡ የዲያስፖራ አባላት የነበራቸውን ቆይታ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዳያስፖራዎች በቆይታቸው የመጡበትን አገራዊ ዓላማ በሚፈለገው መልኩ ማሳካት ችለዋል ነው ያሉት፡፡

በአዲስ አበባ እና በፌዴራል የተለያዩ ተቋማት በጋራና በተናጠል ዳያስፖራውን ያሳተፉ 31 ሁነቶች የተካሄዱ ሲሆን በክልልና በከተማ መስተዳደሮችም እንዲሁ 24 የተለያዩ ሁነቶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ሁነቶች ኢኮኖሚያዊ፣ዲፕሎማሲያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ እንደነበር ገልጸው፤ በዚህም የዳያስፖራው ተሳትፎ  የጎላ ነበር ብለዋል።

በዲፕሎማሲው መስክ ዳያስፖራውን በማሳተፍ "ኢትዮጵያ የግጭት ቀጠና" ሆናለች በሚል ሲሰራጭ የቆየውን የተሳሳተ መረጃ እና ያልተገባ የውጭ አገራት ጫና የቀለበሰ ስራ ማከናወን ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች፣በመዲናዋ የተሰሩ ፓርኮችንና የቱሪስት መስህቦችን በመጎብኘት የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያስተዋውቅ መልዕክት ማስተላለፋቸውንም ተናግረዋል፡፡

ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣትም የኢትዮጵያዊያን የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህል ጎልቶ እንዲታይ አድርገዋል ነው ያሉት፡፡

ወደ አገር ቤት የመጡ ዳያስፖራዎች በጦርነቱ የተጎዳውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ በማደረግ ረገድ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰው፤ በሁለት ወራት ብቻ ከዳያስፖራው 22 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ተችሏል ብለዋል፡፡

ጥሪው በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች የመሰማራት ፍላጎት ኑሯቸው በተለያዩ ምክንያቶች ይህንን ማሳካት ላልቻሉ ዳያስፖራዎች ህልማቸውን እውን እንዲሆን እድል የፈጠረ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ያላቸው የፖለቲካ አመለካከት ሳይገድባቸው አገራቸውን ለማልማት የተዘጋጁበትና ፍላጎት ያሳዩበት ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ወደ አገር ቤት ከመጡ ዳያስፖራዎች መካከል እስካሁን ባለው ሂደት 490 የሚሆኑት በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ስራ መጀመራቸውን አክለዋል።

ኤጀንሲው ወደ አገር ቤት የመምጣት ጥሪ እንዲሳካ ላስተባበሩ ኮሚቴዎች፣የጸጥታ አካላት፣ተቋማት፣መገናኛ ብዙሃን፣ሲቪክ ማህበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም