በወላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ የተከሰተ ጎርፍ በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ

91
ሶዶ ነሀሴ25/2010 በወላይታ ዞን በቦዲቲ ከተማ ከትናትና ማታ ጀምሮ ለረዢም ሰዓት የጣለውን ዝናብ ተከትሎ የተከሰተ ጎርፍ በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ተጎጂዎቹ የከተማ አስተዳደሩና የሚመለከታቸው አካላት ለችግሩ  ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ የከተማው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር ምህረቱ ሞታ ለኢዜአ እንደገለፁት ትናንት ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ጀምሮ የጣለው ከባድ ዝናብ የጎርፍ አደጋን አስከትሏል፡፡ ይኸው ጎርፍ ጫው ካሬ፣ አምባ ሰፈርና ዶጌ ቀበሌ ነዋሪ በሆኑ ከ15 በላይ አባዎራ ቤቶች ውስጥ በመግባት በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ በተለይ ጫው ካሬ ቀበሌ ገጠራማና ተዳፋታማነት በመሆኑ ከ14 ሄክታር በላይ መሬት ላይ በተዘራ የበቆሎ፣ አደንጓሬና ሌሎች ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልፀዋል፡፡ የጎርፍ አደጋው በሰው ህይወት ላይ ያደረሰው ጉዳት እንደሌለም ገልፀዋል፡፡ ፖሊስ ከነዋሪዎች የደረሰውን መረጃ መነሻ በማድረግ ህብረተሰቡን በማስተባበር የነፍስ አድን ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸው የዝናቡ ሁኔታ ቀጣይ ሊሆን ስለሚችል የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቂ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በቦዲቲ ከተማ ምስራቅ ክፍሌ ከተማ ጫዉ ካሬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አበበች ተፈራ በሰጡት አስተያየት ከሌሊቱ 8 ሰዓት አካባቢ በተኙበት ከፍተኛ ጎርፍ ቤታቸውን ሰብሮ በመግባት ውስጥ ባለው ንብረታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ ገልፀዋል፡፡ በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ የነበረው የደረሰ በቆሎና አዲስ  የተዘራ አደንጓሬ በጎርፍ ተጠራርጎ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አቶ መላኩ ገበየሁ በበኩላቸው ከከተማው የሚለቀቀው ጎርፍ እንደዚህ ዓይነት ችግር ሊፈጠር እንደሚችል በተደጋጋሚ ለከተማ አስተዳደሩ ቢያሳውቁም ሰሚ በማጣታችን ምክንያት አደጋው ሊደርስ በመቻሉ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ገልፀዋል፡፡ የከተማዋ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዱባለ ሳህሉ በበኩላቸው  ወደ ኃላፊነት ከመጡ ገና አንድ ሳምንት እንዳልሆናቸው ገልፀዋል፡፡ ሆኖም ግን በከተማው የተሰሩ የውሃ ማፍሰሻ መስመሮች ያልተጠኑና የጥራት ችግር ያለባቸው በመሆኑ ቅሬታዎች እንዳሉ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው ከጥር ጀምሮ እየጣለ ባለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ስጋቶች ስለነበሩ ችግሩን ለመፍታት የቅድሚያ ትኩረት መሆን እንዳለበት ታምኖበት ወደተግባር ለመግባት እየታሰበ ባለበት ወቅት አደጋው በድንገት መከሰቱን ገልፀዋል፡፡ የጎርፍ አደጋው በተለይም ወደ ከተማው የታቀፉ ሶስት የገጠር ቀበሌ የአርሶ አደር ማሳ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ማረጋገጣቸውን ገልጸው የከተማ አስተዳደሩ ጉዳት ለደረሰባቸው ተገቢ ድጋፍ ለማድረግ የልየታ ስራ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በቀበሌዎቹ ከ100 በላይ ነዋሪዎችም በቀጣይ የጎርፍ አደጋ ስጋት ላይ መሆናቸው መለየቱን አስታውቀዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የጎርፍ ማፋሰሻና ማስወገጃ መስመሮችን ለመስራት የወላይታ ልማት ማህበርና የሚመለከታቸው አካላትን በማስተባበር ስራው መጀመሩን አቶ ዱባለ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም