ወጣቱ የሰላምና የአንድነት እሴቶችን ጠንቅቆ በማወቅ ለዘላቂ ሀገራዊ መግባባት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል- ሰላም ሚኒስቴር

61

ሆሳዕና ጥር 29/2014 (ኢዜአ) ወጣቱ ትውልድ በየማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ የሰላምና የአንድነት እሴቶችን ጠንቅቆ በማወቅ ለዘላቂ ሀገራዊ መግባባት የድርሻውን እንዲወጣ ሰላም ሚኒስቴር አስገነዘበ ።

ሚኒስቴሩ ከዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ለ3ኛ ዙር በብሔራዊ በጎ ፍቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ያሰለጠናቸውን ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶች ዛሬ አስመርቋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝምና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን በወቅቱ እንደገለጹት  የብሄራዊ በጎ ፍቃድ ማህበረሰብ ልማት ሰልጣኞች ለሀገራዊና ማህበረሰባዊ ችግሮች የመፍትሄ አካል መሆን አለባቸው ።

ወጣቱ ትውልድ በየማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ የሰላምና የአንድነት እሴቶችን ጠንቅቆ በማወቅ ለዘላቂ ሀገራዊ መግባባት ግንባታ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

ወጣቱ የሀገር ፍቅር ስሜትን ሊያጎለብት እንደሚገባው ጠቁመው ሚኒስቴሩ ይህንኑ ለማጎልበት አላማ ያደረገ በብሔራዊ በጎ ፍቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት መርሀ ግብር ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተልዕኮውን ለማሳካት እንዲያስችለው ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ወጣቶችን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች በልዩ ትኩረትና ቅንጅት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

"ሰልጣኞች ወደ ማህበረሰቡ በሚቀላቀሉበት ወቅት ያለውን አቅም በማስተባበር ለሀገራዊና ማህበረሰባዊ ችግሮች የመፍትሔ ሀሳቦች አመንጭና  የተግባር ስልት ነዳፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል " ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የመንግስት መዋቅርና ማህበረሰቡን በማቀናጀት ለሀገር እድገትና ለአብሮነት መጠናከር እንዲሁም ለሰላም ግንባታ አርዓያ የሚሆኑ ተግባራት የማከናወን ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል ።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው "ሰላም ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ወሳኝና መሰረታዊ ነው" ብለዋል።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የአዕምሮ እርካታ በመፍጠር የሰዎችን የእርስ በእርስ ትስስር በማጎልበት ተኪ የለሌው ሚና የሚጫወት ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ሀገሪቱ እያካሄደች ባለው የሰላም ግንባታ አስተዋጽኦ ለማበርከት ለወጣቶቹ ለ45 ቀን በበጎ በፈቃድ አገልግሎት ምንነትና ውጤቱ፣ በሰላም ግንባታና በየማህበረሰቡ ያሉ ዕሴቶች ማወቅ፤ በስራ ዕድል ፈጠራና  በተለያዩ ጉዳዮች ስልጠና መስጠቱን ተናግረዋል።

ተመራቂዎች ያገኙትን እውነት በመጠቀም ከራስ ወዳድነት ይልቅ ለሌሎች መኖርን በተግባር በማሳየት ተምሳሌት ሊሆኑ እንደሚገባ ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።

ከባሌ ዞን ጎባ ወረዳ የመጣችው ተመራቂ ወጣት ፅዮን ለገሰ በ45 ቀን ቆይታዋ ያገኘችውን በኢትዮጵያዊነት፣ አብሮነትና አንድነት እሴቶችን በመጠቀም የምትቀላቀልበትን ማህበረሰብ ለማገልገል መዘጋጀቷን ተናግራለች።

የኢትዮጵያውያን የአንድነትና አብሮነት እሴቶቻችን ለማጠልሸት የሚደረጉ የተለያዩ ሙከራዎችን ለመቀልበስና ቱባ ዕሴቶች እንዲያብቡ የተቻላትን ሁሉ ለማድረግ በቁርጠኝነት መነሳቷን ገልጻለች ።

በማህበረሰብ አቀፍ በጎ ፈቃድ የልማት አገልግሎት በመሳተፍ ማህበረሰቡን በማገልገል የሚጠበቅባትን ሁሉ ለመወጣት ማዘጋጀቷን ወጣቷ አረጋግጣለች ።

"የአብሮነት እሴቶችን ማጠናከር የሀገሪቱን እድገት ማፋጠን ወሳኝ መሆኑን መረዳቱን የገለጸው ደግሞ  ከጅማ ዞን ሸቤ ወረዳ የመጣው በስልጠናው ተመራቂ ወጣት ጣሂር ናስር ነው ።

በቆይታው ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍል ከተውጣጡ አቻዎቹ ጋር በሀገር ጉዳይ እየመከሩ ባህላቸውን እየተዋወቁና እየተለዋወጡ እንዲሁም በጋራ ማደግ ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች ሀሳቦች እየተላዋወጡ  ሰፊ ግንዛቤና ልምድ መቅሰማቸውን ይገልጻል።

በተለይ ወጣቱ ክፍል ከስሜታዊነትና ከዘረኝነት አስተሳሰብ በመውጣት በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በመሳተፍ የህዝቡን የእርስ በርስ ትስስር  ማጠናከርና ጠንካራ አንድነት መገንባት ላይ ማተኮር እንደሚገባው አመልክቷል።

በስልጠናው ያገኘውን ዕውቀትና ልምድ በመጠቀም በተለያዩ አካባቢዎች በበጎ ፈቃድ ልማት ስራዎች በመሳተፍ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል ።

በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ  የዩኑቨርሲቲው ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የሀዲያ ሀገር ሽማግሌዎችና ተማሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም