በክልሉ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማልማት የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል እየተሰራ ነው

84


ጥር 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ያሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን አልምቶ በመጠቀም የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል በደብረማርቆስ ከተማ በአራት ወንድማማቾች የተገነባውን "እቴ" ግራናይት ፋብሪካ ዛሬ መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
ዶክተር ይልቃል በምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ እንደሉት ክልሉ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎች ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችል እምቅ ሃብት አለው።
የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማጥናት ለባለሃብቶች ክፍት በማድረግ ዘርፉን የስራ እድል መፍጠሪያና የገቢ ማስገኛ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ የተመረቀው የግራናይት ፋብሪካም እስካሁን ያልተነካውን የክልሉ የማዕድን ልማት በማፋጠን የህዝባችን ኑሮ ለማሻሻል ያደረግነው ጥረት ውጤት ነው ብለዋል።
የማዕድን ዘርፉን በማልማት የክልሉን ኢኮኖሚ ለማፋጠን ዘርፉን የሚመራውን የማዕድን ኤጀንሲ ወደ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ማሳደጋቸው ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።
የክልሉን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለመጨመርና ለባለሃብቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በአገልግሎት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ነቅሶ ለማረም የሚያስችሉ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የአካባቢው ማህበረሰብ ጉዳት እንዳይደርስበት የክልሉ መንግሥት ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር ይሰራልም ብለዋል።
የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሌ አበበ እንዳሉት ክልሉ በኮንስትራክሽን፣ በጌጣጌጥና ሌሎች አምሰት ዘርፎች 33 የማዕድን አይነቶች እምቅ ሀብት እንዳለው በጥናት ተረጋግጧል።
የማዕድን ዘርፍ በክልሉ ተረስቶ የኖረውን የማዕድን ሀብት በማበልፀግ ለሀገር ዕድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት ለማዋል አሁን ላይ ባለሃብቶችን መሳብ ላይ ያተኮረ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከፋብሪካው አራት ወንድማማቾች ባለቤቶች መካከል አቶ ሲሳይ አያልነህ እንዳሉት ፋብሪካውን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 360 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጓል።
ሀገራችን በየዓመቱ 27ሺ ቶን የግራናይት ምርት ከውጭ በማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ታጣለች ያሉት አቶ ሲሳይ ዛሬ የተመረቀው ፋብሪካ እስከ 6ሺህ ቶን በዓመት በማምረት ወጪው ለማዳን እገዛ ያደርጋል።
"እቴ" ግራናይት ፋብሪካ 5ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ የተገነባ ሲሆን፤ ለ350 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ ከንቲባ አቶ ይትባረክ አበበ በበኩላቸው በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በግብርና፣ በማዕድንና ሌሎች ዘርፎች ማልማት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች የከተማ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም