የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም እና በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽዖ ላበረከታችሁ ምስጋና ይድረስ!

115

ጥር 29/2014 የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በመዲናችን አዲስ አበባ እንዲደረግ የአባል ሀገራት መሪዎች መወሰናቸውን ተከትሎ ወንድማዊ አጋርነት የታየበት የኅብረቱ ጉባኤ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት ተካሂዶ በስኬት ተጠናቅቋል።

የኅብረቱ ጉባኤ ፍሬያማ ውይይት የተካሄደበት፣ ለአህጉራችን የሚጠቅሙ ውሳኔዎች የተላለፉበት፣ ከምንም በላይ ወንድማዊ አጋርነት የታየበት ነበር ማለት ይቻላል።

እውነተኛ ወዳጅነት የሚመዘነው በችግር ጊዜ እንደመሆኑ መጠን፣ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ ወዳጅ ስትፈልግ ከማንም ቀድማችሁ ደርሳችሁልናል።

ሌሎች ሲሸሹን ከጎናችን በመቆም እውነተኛ ወዳጅነታችሁን አስመስክራችኋል።ለዚህም ኢትዮጵያ ከልብ ታመሰግናችኋለች። አፍሪካውያንን አንድ የሚያደርገን የአንድ አህጉር ሕዝቦች ወይም የአንድ ምድር ልጆች መሆናችን ብቻ አይደለም።ከወንዞቻችን በላይ ታሪካዊ ሁነቶች ይበልጥ ያስተሣሥሩናል፤ ከመልክአ ምድሩና ከአየር ንብረቱ በበለጠ የምንጋፈጣቸው ችግሮች ያመሳስሉናል።

በክፉም በደጉም አብረን ነበርን፤ ወደፊትም አብረን እንዘልቃለን።ዕጣ ፈንታዎቻችን ተመሳሳይ ናቸው። የአንዳችን ቁስል ሌላችንን ማመሙ፤ የአንዳችን ሰቀቀን ለሌላችን መሰማቱ ጥብቅ ቤተሰቦች አድርጎናል። የወዳጅነታችን መሠረቱ ጥቅም ሳይሆን እውነተኛ ወንድማማችነት ነው።

ትናንት ቀደምቶቻችን በጀመሩት አንድነት፣ ዛሬ ጠብቀን ባቆየነው ኅብረት፣ እና ነገ እውን በሚሆነው የተግባር ቅንጅት የአፍሪካ ክብር ከፍ ይላል፤ በዓለም መድረክ ድምጻችን ጎልቶ መደመጥ ይችላል። “ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ” የመፈለግ ጉዟችን ሁላችንንም ከስኬት ጫፍ እንደሚያደርሰን ምንም ጥርጥር የለውም።በመንገዱ ላይ ዕንቅፋት ይገጥመን ይሆናል፤ ፈተናዎች ዕረፍት አልሰጥ ብለው እንቸገር ይሆናል፤ ነገር ግን እጅ ለእጅ ተያይዘን እናልፈዋለን።

ዛሬ የተሻገርነው ፈተና ለእኛ ትምህርት፣ ከእኛ በኋላ ለሚመጣው ትውልድ የጥንካሬ ምንጭ መሆኑ አይቀርም።የኅብረቱ ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩ ብዙዎች ናቸው። እንግዶቻችን በሰላም ወደ ሁለተኛ ቤታቸው አዲስ አበባ መጥተው ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲቆዩ የጸጥታ ኃይሎች በሚገባ ኃላፊነታቸውን ተውጥተዋል።

ጉባኤው ምንም ዓይነት ችግሮች እንዳይገጥሙትና የጉባኤው ተሳታፊዎች በከተማዋ ምቾት ያለው ቆይታ እንዲኖራቸው ለማስቻል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያሳየው ትጋት፣ የከተማው ነዋሪዎች ያሳዩት ትዕግሥትና ተባባሪነት፣ ሆቴሎችና አገልግሎት ሰጪዎች ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተላበሰ መንገድ ለማስተናገድ ያደረጉት ደፋ ቀና የሚደነቅ ነው።

የሚዲያ ባለሞያዎች ጉባኤው ተደራሽ እንዲሆን የፈጠሩት ቅንጅት ውጤታማ ነበር። ጉባኤውን በንቃት የመሩትን የኅብረቱን ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ጨምሮ ለጉባኤው ስኬት አስተዋጽዖ ያበረከቱ አካላትን ኢትዮጵያ ታመሰግናለች።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ጥር 29 ቀን 2014 ዓ.ም.


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም