ለህግ የበላይነት መከበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ በባሌ ሮቤ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

52
ጎባ ነሀሴ 25/2010 መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየወሰዳቸው ያለውን የእርምት እርምጃ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በባሌ ሮቤ ከተማ አስተያየታቸወን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ በተለይ ቄሮዎች በስማቸው እየተንቀሳቀሱ አፍራሽ ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን ሴራ በማጋለጥ በአዲሱ ዓመት ሰላምና ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥ በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም ተጠቁሟል፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል ሼህ ሀሰን ኡሰማን ለኢዜአ እንደተናገሩት መንግስት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አሰተዳደር ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ  ነው፡፡ በሀገሪቱ እየመጣ ያለው  ለውጥ እንዲቀለበስ  የሚሯሯጡ ኃይሎችን አሳልፎ በመስጠት የህግ የበላይነት እንዲከበር መንግስት እየወሰዳ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡ ሌላው ነዋሪ  አቶ ኡመር ከዲር በበኩላቸው"  ወጣቱ ሀይል በሀገሪቱ ተንሰራፍቶ የነበረውን ብልሹ አሰራሮችና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄዶችን እንዲስተካከሉ የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ለውጡ እንዲመጣ ግንባር ቀደም ተወናይ ነበር " ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቄሮ ሽፋን ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን በማድረግ የዜጎች ህገ መንግስታዊ መብቶች ጭምር ጥያቄ ወስጥ ለማስገባት  የሚሞክሩ ህገወጥ ቡድኖችን አጥበቀው  እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡ አቶ ኡመር እንዳሉት የመደመርና የይቅርታ እሳቤ የሚደነቅ ቢሆንም የዜጎችን ሰብዓዊና ህገ መንግስታዊ መብቶችን በማስከበር በኩል የታዩ ክፍተቶችን በማረም ህገ ወጦች ለህግ ቀርበው ውሳኔ እንዲያገኙ መደረግ አለበት፡፡ መንግስት በህገ ወጦች ላይ እየወሰዳ ያለው የእርምት እርምጃ የሚደነቅና ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ያመለከተችው ደግሞ  ወጣት ሀሊማ ተማም ናት፡፡ ወጣቶችም በአዲሱ ዓመት በስማቸው የሚነግዱ ቡድኖችን ሴራ በማጋለጥ ለሰላምና ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ ላይ ትኩረት አድርገው መንቀሳቀስ እንደለባቸውም ጠቁማለች፡፡ እንደ ወጣቷ ገለጻ፤ ወጣቱ በሀገሪቱ ተንሰራፍቶ የነበረውን ብልሹ አሰራሮችን ለመናድ ባደረገው ተጋድሎ ያስመዘገበውን ድል ለሀገሩ ሰላምና አንድነት ዘብ በመቆም መድገም አለበት ፡፡ ወጣት አህመድ በከር እንዳለውም በከተማው የተደራጁ ቄሮዎች  ከኃይማኖት አባቶችና አባ ገዳዎች ጋር በመቀናጀት ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ የሚያደርጉት በመደገፍ የድርሻቸው ለመወጣት ዝግጁ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ቦታዎች በቄሮዎች ሰም የሚንቀሳቀሱ አፍራሽ አካላት እየፈጸሙ የሚገኙት አስነዋሪ ተግባር ሰላም ወዳዱን ወጣት የማይወክልና የሚወገዘ ተግባር መሆኑንም ጠቅሷል፡፡ መንግስት በስማቸው የሚነግዱ አፍራሽ አካላትን ለህግ ማቅረብ መጀመሩ የሚበረታታ መሆኑን ያመለከቱት አስተያየት ሰጪዎቹ የእርምት እርምጃው ቀጣይነት ኖሮት የህግ የበላይነት እንዲከበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም