በህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የበርካታ አገራት መሪዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች መገኘታቸው የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ለመላው ዓለም የሚያሳይ ነው

53

አዲስ አበባ፤ ጥር 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የበርካታ አገራት መሪዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች መገኘታቸው የኢትዮጵያን ሰላማዊ ነባራዊ ሁኔታ ለመላው ዓለም የሚያሳይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ብርቱካን አያኖ ገለጹ።

በዛሬው እለት በአዲስ አበባ የተጀመረው 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ መልኩ በመከናወን ላይ ይገኛል።

በጉባኤው ለመሳተፍም የበርካታ አገራት መሪዎች እና ልዑካኖቻቸው እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ብርቱካን አያኖ፤ በህብረቱ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የመጡ እንግዶችን በጥሩ መስተንግዶ አቀባበል መደረጉን ገልጸዋል።

በመሆኑም በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የበርካታ አገራት መሪዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች መገኘታቸው የኢትዮጵያን ሰላማዊ ነባራዊ ሁኔታ ለመላው ዓለም የሚያሳይ ነው ብለዋል።

አቀባበሉን ደማቅና የተሳካ ለማድረግ በርካታ ተቋማት ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።

የአገራት መሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እና የሚዲያ ባለሙያዎች አዲስ አበባ መገኘታቸው የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ለማስተዋወቅ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

በመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ ለገቡ አካላት አቀባበል የሚያደርጉ ሚኒስትሮች ኢትዮጵያን በሚመለከት ገለፃ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው እንግዶቹም በተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ደስተኞች ስለመሆናቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም