በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ለአፍሪካ ልማት የሚተጋ ጠንካራ የፋይናንስ ተቋም መገንባት አለብን

51

ጥር 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) በፓን አፍሪካኒዝም የትብብር መንፈስ ለአፍሪካ ልማት የሚተጋ ጠንካራ የፋይናንስ ተቋም መገንባት አለብን ሲሉ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር የሆኑት የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንትና ማኪ ሳል ጥሪ አቀረቡ፡፡

በ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል አዲሱ የህብረቱ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡ ሲሆን፤ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግርም አፍሪካዊያን ቁርጠኛ ሆነው በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

"የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ለህብረቱ ጉባኤ ታዳሚዎች ደማቅ አቀባበል ማድረጓንም ነው ያነሱት፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ኢትዮጵያ የነበራት ተሳትፎ የጎላ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

አፍሪካውያን በድርቅ፣ በአንበጣ መንጋ፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በውስጣዊ ግጭትና ሽብርተኝነት እየተፈተኑ መሆኑንም ነው ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል የገለጹት፡፡

እነዚህ ችግሮች በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትሉትን ተጽእኖ ለመቋቋም ደግሞ ለአፍሪካ ልማት የሚሰራ ጠንካራ የፋይናንስ ተቋም መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት አፍሪካ ተገቢውን ውክልና ታገኝ ዘንድ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ በጋራ ድምጻችንን ማሰማት አለብን  ነው ያሉት፡፡

በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በደረሰው ሰብዓዊ ቀውስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች ስራ-አጥ ሆነዋል፤ በርካቶች ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል ብለዋል፡፡

እነዚህ ተጎጂዎችን ወደ መደበኛ ህይወታቸው ለመመለስ ደግሞ አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ መኖር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ አፍሪካውያን ለአንድነታችን ቁርጠኛ በመሆን የአፍሪካ ልማት ፕሮጀክቶችን ገቢራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው የገለጹት፡፡

"የአፍሪካ እጣፈንታ በእጃችን ነው" ያሉት ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል፤ በዚህም በተባበረ ክንድ የፋይናንስ ተቋሞቻችንን ማሳደግ፣ የልማት ፕሮጀክቶችን ደግሞ በጋራ መገንባት አለብን ብለዋል፡፡

"መለያየት አንድነታችንን ያላላል፤ እድገታችንንም ያዘገያል" ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

እንደ ቻይና አፍሪካ ያሉ ዓለም አቀፍ ትብብሮችን ከዚህ በላይ ማሳደግ እንደሚገባም ነው የአፍሪካ ህብረት አዲሱ ሊቀመንበርና የሰኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም