የአፍሪካ ድምጽ የሚሰማበት፣ የፓን አፍሪካዊነት ድምጽ የሚጎላበት የጋራ አህጉራዊ ሚዲያ ሊኖረን ይገባል

79

አዲስ አበባ፤ ጥር 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) "የአፍሪካ ድምጽ የሚሰማበት፣ የፓን አፍሪካዊነት ድምጽ የሚንጸባረቅበት የጋራ አህጉራዊ ሚዲያ ሊኖረን ይገባል" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይህን ያሉት በ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህን ወቅት አፍሪካ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ የምትሳልበት አግባብ አሉታዊ እንደሆነ አንስተዋል።

እነዚህ ሚዲያዎች ሆነ ብለው አፍሪካን የድርቅ፣ ርሃብ፣ ቸነፈርና ኋላቀርነት ምልክት አድርገው እንደሚስሏት ገልጸው፤ ይህን የተሳሳተ ትርክት ለመለወጥ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ሲሉ አንስተዋል።

በመሆኑም የአፍሪካን ገጽታ የሚገነባ አፍሪካዊ ሚዲያ ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

አፍሪካ በዓለም አቀፍ ተቋማት ባለመወከሏ በትክክል ድምጿ እንዳልተሰማ ሁሉ፤ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አፍሪካን የሚስሉበት መንገድ በተሰላ ስትራቴጂ በሚመስል በአሉታዊ መልኩ እንደሆነ አንስተዋል።

"ይህ ተገቢ ያልሆነ አፍሪካን ገጽታ የማጠልሸት ተግባር መለወጥ አለበት" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአፍሪካዊያን ድምጽ የሚያስተጋባ፣ የፓን አፍሪካዊነት መንፈስ የሚንሰጸባረቅበት የጋራ ሚዲያ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአፍሪካን ገጽታ የማጠልሻት አካሄድ በመለወጥ የአፍሪካዊያን አጀንዳ የሚሰራጭበት የፓን አፍሪካ ድምጽ የሆነ ሚዲያ እንዲቋቋም ለህብረቱ ጉባኤ ተሳታፊዎች ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም