የእጩ ኮሚሽነሮች የጥቆማ ሂደት ኢትዮጵያን ከችግር ሊያሻግሩ ይችላሉ ተብሎ የሚታመንባቸው በርካታ ግለሰቦች መኖራቸውን ያስገነዘበ ነው

69

አዲስ አበባ፣  ጥር 28/2014(ኢዜአ) ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የእጩ ኮሚሽነሮች የጥቆማ ሂደት ኢትዮጵያን ከችግር ሊያሻግሩ ይችላሉ ተብሎ የሚታመንባቸው በርካታ ግለሰቦች መኖራቸውን ያስገነዘበ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን እጩ ኮሚሽነሮችን የምርጫ ሂደት አስመልክቶ ከኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል።

ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነርነት 632 ግለሰቦች ተጠቁመው 42 ሰዎች ተለይተው በስም ዝርዝር ይፋ ተደርጓል።

ጉዳዩን አስመልክቶ ከተለያዩ አካላት ጋር በተደረገው ውይይት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የሰለጠነ ብሔራዊ ምክክር በማራመድ የተሻለች ኢትዮጵያን ማስቀጠል ይገባናል ብለዋል።

የምክክር ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን መላ ኢትዮጵያዊያን አዎንታዊ ሚና ሊኖራቸው ይገባልም ነው ያሉት።

ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የእጩ ኮሚሽነሮች የጥቆማ ሂደት ኢትዮጵያን ከችግር ሊያሻግሩ ይችላሉ ተብሎ የሚታመንባቸው በርካታ ግለሰቦች መኖራቸውን የተገነዘብንበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን አንድ የሚያደርጓቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን በመገንዘብ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አዋጅ ቁጥር 1265/2014 ውይይት ከተካሄደበት በኋላ መጽደቁን አስታውሰዋል።

አዋጁ ከጸደቀ በኋላም የምክክሩ "እጩ ኮሚሽነሮችን የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ማን ይቀበል" የሚለው ጉዳይ ሰፊ ክርክር ከተደረገበት በኋላ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀበል መደረጉን ጠቅሰዋል።

የእጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማን ምክር ቤቱ ከተቀበለ በኋላም የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት፣ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ጥምረት መሪ በአማካሪነት እንዲካተቱ ተደርጓል ብለዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የጥቆማ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ሄኖክ ስዩም፤ በእጩ ኮሚሽነርነት የተለዩትን የ42 ግለሰቦች ስም ዝርዝር እና የስራ ልምድ ለውይይት መነሻነት አቅርበዋል።

በእጩነት የተመረጡ ግለሰቦችን በሚመለከት በምክር ቤቱ የፌስቡክና ዌብ-ሳይት ማንኛውንም ገንቢና የተቃውሞ አስተያየት መስጠት እንደሚችል አመላክተዋል።

በምክክር መድረኩ የተሳተፉት አካላትም የጥቆማ ሂደቱን አድንቀው የዕጩ ኮሚሽነሮች ምርጫ የወጣቶች እና ሴቶችን ስብጥር ያማከለ እንዲሆን ቢደረግ ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ በሰጡት ማብራሪያ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን እጩ የኮሚሽነሮች መረጣና ጥቆማ ሂደት ብዝሃነትን፣ የስራ ልምድን ብቃትና ሌሎች ወሳኝ  መስፈርቶችን ያማከለ እንዲሆን ሰፊ ሰራ ተሰርቷል ብለዋል።

አገራዊ ምክክሩ ስኬታማና ውጤታማ ሆኖ የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በየደረጃው የሚገኝ የኃይማኖት መሪ፣ የፖለቲካ ድርጅት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅት መሪ እና መላ ኢትዮጵያዊያን ወሳኝ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመ ሲሆን በቀጥታ በተደረገው የህዝብ ጥቆማ በሚመረጡት 11 ኮሚሽነሮች የሚመራ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም