የከተማችን ነዋሪዎች የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ስኬታማ በማድረግ በኩል ያላችሁ ሚና እጅግ በጣም ትልቅ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

241

ጥር 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) ውድ የከተማችን ነዋሪዎች የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ስኬታማ በማድረግ በኩል ያላችሁ ሚና እጅግ በጣም ትልቅ ነው ¬ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዛሬ የሚጀመረው 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና ከትናንት በስቲያ የተጠናቀቀው 40ኛው የህብረቱ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በስኬት እንዲካሄድ የከተማዋ ነዋሪዎች እያደረጉ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

ነዋሪው እስካሁን እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ ጉባኤው እስኪጠናቀቅና እንግዶች ወደየመጡበት አገር እስኪመለሱ ድረስ የተለመደ ትብብሩንና እንግዳ ተቀባይነቱን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያዊ ጨዋነት በያላችሁበት እንግዳ በማስተናገድ ትልቁ ባህላችን ሁሉንም በየአካባቢው ውብና ድንቅ አድርጋችሁ እንደምታስተናግዱ እምነቴ የፀና ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ የከተማችን ነዋሪዎች ይህን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ስኬታማ በማድረግ በኩል ያላችሁ ሚና እጅግ በጣም ትልቅ ነው ብለዋል።

በተለያየ መንገድ ከፀጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት በከተማዋ የሰላምና ፀጥታ ስራ በመሳተፍ ስታደርጉ የነበረውን ጥረት አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉና ትኩረታችሁን እንደ ወትሮው እንድታደርጉ እያሳሰብኩ፣ ጉባኤው ስኬታማ እንዲሆን የበኩላችሁን እንድትወጡ ከአደራ ጭምር እጠይቃለሁ ሲሉ አሳስበዋል።

ዛሬ ለሚጀመረው 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶችና ሌሎች የጉባኤው ተሳታፊዎች አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የከተማዋ ነዋሪዎች እንግዶቹ ያማረ ቆይታ እንዲኖራቸው ሰፊ ዝግጅት ማድረጋቸውም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም