በፈንታሌ-ቦሰት ወረዳ በተፈጸመው የግድያ ወንጀል ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ እያጣራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

121

ጥር 26/2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ-ቦሰት ወረዳ በንጹሃን ዜጎችና በፀጥታ ኃይሎች ላይ ተፈጽሞ ከነበረው የግድያ ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ እያጣራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራና ፍትህ ማስፈን ዘርፍ  ኃላፊ  ግርማ ገላን ዛሬ በሰጡት መግለጫ ባለፈው ህዳር ወር መገባደጃ ላይ በ14 ንጹሃን ዜጎችና በ11 የክልሉ ፖሊስ አባላት ላይ የተፈጸመውን የግድያ  ወንጀል ፖሊስ በትኩረት በመከታተል አስፈላጊውን ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ መግለጫ ጉዳዩ እስካሁን ለሕዝብ ይፋ ያልተደረገው የምርመራ  ሂደቱ ያልተጠናቀቀና በሂደት ላይ ያለ በመሆኑ ነው።

ፖሊስ  የምርመራ  ሂደቱን እንዳጠናቀቀ  ውጤቱን ለህዝብ በይፋ እንደሚያሳውቅ ምክትል ኮሚሽነሩ  በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ምክትል ኮሚሽነር  ግርማ እንዳሉት፤ ጉዳዩ በሂደት ላይ ቢሆንም አሁን መግለጫ መስጠት ያስፈለገው በተለይ  በአንዳንድ ወገኖች በማህበራዊ  ሚዲያ  እየተሰራጩ  ያሉ መረጃዎችን ግልፅ ለማድረግ ነው።

የሕግ የበላይነት በሁሉም ላይ ተፈጻሚ እንደሚደረግ ገልጸው፤ የሰውን ህይወት ያጠፋ ማንኛውም ኃይል  ለሕግ  ቀርቦ ተጠያቂ  እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም