አፍሪካውያን የጋራ የህዋ ሳይንስ አሰሳ ስርዓት በመገንባት አህጉራዊ ሉዓላዊነታቸውንና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን ማስከበር አለባቸው

111

ጥር 26/2014/ኢዜአ/ አፍሪካውያን የጋራ የህዋ ሳይንስ አሰሳ ስርዓት በመገንባት አህጉራዊ ሉዓላዊነታቸውንና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን ማስከበር እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

የህዋ ሳይንስ የቀጣዩ ትውልድ የሀብት ምንጭና የመወዳደሪያ ሜዳ እየሆነ በመምጣቱ ታላላቅ ኩባንያዎች ጭምር የህዋ ሳይንስ ምርምር ፕሮጀክቶችን ጀምረዋል ብሏል፡፡

በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ፣ ሞሮኮ፣ አልጀሪያና ኬንያ ውጭ አብዛኞቹ ሀገራት የህዋ ሳይንስ ፕሮግራም አልጀመሩም፡፡

የአፍሪካን የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ በአፍሪካ ህብረት ጉባኤ "የአፍሪካ ስፔስ ፖሊሲና ስትራቴጂ" ተቀርፆ ጸድቋል፡፡

የአፍሪካን ስፔስ ሳይንስ ፕሮግራም የሚያስተባብር ተቋም በግብጽ ርዕሰ መዲና ካይሮ የተቋቋመ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ውጤት አላመጣም ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ ለኢዜአ እንዳሉት፣ አፍሪካ በህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከዚህ ግባ የሚባል ጥቅም እያገኘች አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ ሁለት የመሬት ምልከታ ሳትላይቶችን በማምጠቅ፣ ሁለት ባለ አንድ ሜትር ኦፕቲካል ቴሌስኮፖችን በመገንባት እንዲሁም የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያ በመገንባት ከምስራቅ አፍሪካ ብሎም ከአህጉሪቱ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2016 የህዋ ሳይንስና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዮትን በተሻለ አደረጃጀት ብትጀምርም አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

አፍሪካውያን አሁን ባለው የዲጅታል ዘመን የዳበረ የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስርዓት መገንባት ካልቻሉ አህጉራዊ አንድነታቸውንና ሉዓላዊነታቸውን ማስጠበቅ ሊሳናቸው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ አፍሪካውያን በትብብር ጠንካራ የህዋ ሳይንስ አሰሳ ስርዓት በመገንባት የቀጣዩን የዲጂታል ቴክኖሎጂ  ስርዓት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት  በተናጠል ግዙፉን የህዋ ሳይንስ አሰሳ ስርዓት ለመገንባት ሊቸገሩ እንደሚችሉ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በመተባበር አህጉራዊ የሆነ የህዋ ሳይንስ የአሰሳ ስርዓት መገንባት ይቻላል ብለዋል፡፡

ለአብነት አፍሪካውያን የሚጠቀሙባቸው "ጂ ፒ ኤስ እና ግሎናስ" የሚባሉ የህዋ ሳይንስ የአሰሳ ስርዓቶች በሌሎች ሀገራት የለሙ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አፍሪካውያን የቀጣዩ የሉዓላዊነትና የሀብት ምንጭ የሆነውን የህዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂ በጋራ በማልማት ለትውልድ ማሻገር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

"ህዋ ቀጣዩ ዋናው የሀብት ምንጭ ቢሆንም ከመቶ ኪሎ ሜትር ርቀት በኋላ የማንም ሀብት አይደለም ባለቤት የለውም" የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ቀድሞ የያዘ ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ትልቁ የመወዳደሪያ መስክ በመሆኑ በዘርፉ የዳበረ ልምድና አቅም ያላቸው ሀገራት በሰፊው ሊቆጣጠሩት እንደሚችሉ መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡

በመሆኑም አፍሪካውያን ከወዲሁ በትብብር በመስራት በህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን አቅም መገንባት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

አፍሪካውያን በጋራ በመቆምና በመተባበር ግዙፍ የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል በመገንባት አህጉራዊ ሉዓላዊነታቸውንና ጥቅማቸውን ማስከበር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የህዋ ሳይንስ የቀጣዩ ትውልድ የሀብት ምንጭና ሀያልነትን ለማሳየት የመወዳደሪያ ሜዳ እየሆነ በመምጣቱ ታላላቅ ኩባንያዎች ጭምር የህዋ ሳይንስ ምርምር  ፕሮጀክቶችን ጀምረዋል ብለዋል፡፡

ጉግል፣ አማዞን፣ ፌስቡክና መሰል የዓለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች የህዋ ሳይንስ ምርምር ፕሮጀክቶችን በመጀመር ዘርፉን በስፋት እየተቀላለቁ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

አፍሪካውያን ድምፃቸውን በጋራ በማሰማት በጋራ ሰርተው ቀጣዩ ትውልድ የዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም